የልማት ባንክ የማይመለስና አጠራጣሪ ብድር 18.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል
በሦስት ወራት 344 ሚሊዮን ብር መክሰሩ ተገልጿል
በቀጣዮቹ ወራት በተለየ ሁኔታ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ካልተገኘ በስተቀር፣ ከነዳጅና ከመድኃኒት ግዥ በዘለለ የኢኮኖሚውን ፍላጎት ማስተናገድ እንደማይቻል የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ መጋቢት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።
የባንኩ ገዥ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ስምንት ወራት አገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ሸቀጦችና አገልግሎቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 1.64 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አመልክተዋል።
በተጠቀሱት ወራት ከወጪ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው መጠን ጋር ሲነፃፀር በ9.4 በመቶ ያነሰ እንደሆነ ገልጸዋል። ከግለሰቦችና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተላከ የሐዋላ ገቢ በአጠቃላይ 3.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ አስረድተዋል።
በተቃራኒው ባለፉት ስምንት ወራት አገሪቱ ከውጭ ለምታስገባቸው ምርቶች 10.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉን፣ ይህም ወጪ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ1.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
በተጠቀሱት ወራት ከወጣው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ለነዳጅ ግዥ የተከፈለው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አስታውቀዋል።
በተጠቀሱት ወራት ወደ አገር ለገቡ ሸቀጦች የተከፈለው የውጭ ምንዛሪና ወደ ውጭ ከተላኩ ሸቀጦች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ መሀል የ8.9 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ሚዛን ጉድለት እንደሚታይ የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የተገለጸው ጉድለት የተሸፈነው ከአገልግሎት (በዋናነት ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት)፣ ከውጭ በሐዋላ ከተላከ ገቢና ከውጭ ከተገኘ ዕርዳታና ብድር መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለው መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት የ2.6 ወራት ፍላጎትን ለመሸፈን ብቻ የሚበቃ እንደሆነ ገልጸዋል።
የንግድ ማኅበረሰቡ የውጭ ምንዛሪ በተመለከተ የሚያቀርበውን እሮሮ በመጥቀስ የምክር ቤቱ አባላት ስለመፍትሔው ማብራሪያ የጠየቁ ሲሆን፣ የባንኩ ገዥ በሰጡት ምላሽ በአሁኑ ወቅት ያለው የውጭ ምንዛሪ መጠን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማንቀሳቀስና የግሉን ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ እየዋለ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከተለያዩ አገሮች ጋር ተነጋግረው ማምጣት የቻሉት 2.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እንደተገኘው የውጭ ምንዛሪ ተመሳሳይ ጥረት ተደርጎ በቀጣዮቹ ወራት ተመሳሳይ ሀብት ካልተገኘ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ እንደማይቻል ገልጸዋል።
“ይህ ካልሆነ ልናደርግ የምንችለው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅና ለመድኃኒት ግዥ ብቻ በጥንቃቄ ማዋል ነው፤” ብለዋል። ከዚህ በመለስ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ የአምስትና የአሥር ዓመታት ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ ቀን ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ መንበረ ሥልጣን ሲመጡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አረንቋ ውስጥ ወድቆ እንደገጠማቸው ገልጸዋል።
ኃላፊነቱን በተቀበሉ በሳምንቱ የቀረበላቸው የ20 ቢሊዮን ብር የደመወዝ ጥያቄ እንደነበርና ይህንን የአገሪቱ አቅም መመለስ እንዳልቻለ፣ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ቆሞ አገሪቱን ለተጨማሪ የሀብት ብክነት ሰለባ አድርገዋት እንደነበር አስታውሰዋል።
ችግሩን ለማስተካካል ባከናወኗቸው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ተግባራት ኢንቨስትመንትንና ትንንሽ ብድሮችን ሳይጨምር ሦስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ማግኘት እንደቻሉ፣ አገሪቱ የተበደረቻቸውን ግዙፍ የውጭ ብድሮች ክፍያ መፈጸም ባለመቻሏ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ቀድሞ ለመከላከል ከቻይና መንግሥት ጋር ባደረጉት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ፣ መከፈል የተጀመረው ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ብድር የመክፈያ ጊዜ በሰፊ ርቀት እንዲራዘም መቻሉን መግለጻቸው ይታወሳል።
የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ያነሱት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገባበትን አጣብቂኝ የተመለከተ ነበር።
በተሰጠው ተልዕኮና ተግባራቱ ምክንያት ባለሙያዎች የፖሊሲ ባንክ በማለት የሚገልጹትና ከመቶ ዓመታት በላይ የአገልግሎት ቆይታው የሚታወቀው ልማት ባንክ፣ በኪሳራ ውስጥ መውደቁንና በፍጥነት መታደግ ካልተቻለ ህልውናውን ሊያጣ እንደሚችል ይናገር (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ገዥው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2011 በጀት ዓመት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 46.17 ቢሊዮን ብር ሆኖ ተመዝግቧል።
ከዚህ ውስጥም የማይመለስና አጠራጣሪ ብድሩ የአጠቃላይ ብድሩን 39.45 በመቶ እንደደረሰ ይፋ አድርገዋል። ይህም ማለት ልማት ባንክ ካበደረው አጠቃላይ ብድር ወስጥ 18.1 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ሊመለስ የማይችልና መመለሱ አጠራጣሪ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም ባንኩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ 344 ሚሊዮን ብር እንደከሰረ፣ ለምክር ቤቱ አስታውቀዋል፡፡
የማይመለስና መመለሱ አጠራጣሪ ከሆነው የባንኩ ብድር ውስጥ ዋነኛውን ድርሻ የሚይዘው ለሰፋፊ እርሻዎች የተሰጠው ብድር እንደሆነ የተናገሩት ገዥው፣ አብዛኞቹ ተበዳሪዎች የተበደሩትን ገንዘብ ለሌላ ዓላማ እንዳዋሉትና የእርሻ መሬቱ በሚገኝበት አካባቢ የጥበቃ ቤት እንኳን ያልገነቡ መኖራቸውን ገልጸዋል።
ተበዳሪዎቹን ተከታትሎ ለሕግ ማቅረብ እንደሚገባ የገለጹት ይናገር (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን ባለው ቁመና ብድሮቹን የማስመለስም ሆነ በኢኮኖሚው ውስጥ የተሰጠውን ተልዕኮ የመወጣት አቅም እንደሌለው ተናግረዋል።
በመሆኑም ባንኩን አፍርሶ እንደገና መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን በራሱ ጊዜ በቅርቡ ሊጠፋ እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህ ከመሆኑ በፊት መፍትሔ ለመስጠት ኮሚቴ ተዋቅሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።