አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባደረገው ስብሰባ የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በተዘጋጀ ረቀቅ አዋጅ ላይ መክሮ እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።
ምክር ቤቱ የካቢኔ አባላት ቁጥርን ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ተወስኗል።
በዚህም መሰረት ዋና ዋናዎቹ ለውጦቹ፦
የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲሆን
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው- የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሆን
የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው- የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን ወስኗል።
ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ እንደተሰጠባቸውም አቶ ፍፁም ገልፀዋል።
ሌላው ቁልፍ ውሳኔ በሀገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ “የሰላም ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ተወስኗል።
ከትምህርት ሚንስቴር ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመውሰድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር” ተብሎ እንዲደራጅ ተወስኗል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ሁለት ተቋማት ሆነው እንዲደራጁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።
እንዲሁም በአዲሱ አደረጃጀት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ቀርቶ በቀጣይነት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሰረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል።
ይህም የመንግሥት ቁልፍ ሚና የሆነው ሬጉሌሽን (ቁጥጥር) በልማት ድርጅቶች ላይ ካለው የባለቤትነት ሚና ተለይቶ እንዲታይ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
ረቂቅ አዋጁ ሌሎች መለስትኛ ለውጦችንም የያዘ ሲሆን፥ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ፍፁም ያስታወቁት።