አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ድርድር መጀመሩን የኢፌዴሪ መንግስት ገለጸ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለጣቢያችን በላከው መግለጫ፥ የኢፌዴሪ መንግስት የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ ያለሰለሰ ጥረትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቅሷል።
የሃገሪቱን ህገ መንግስት ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን በገለጸው መሰረት፥ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሷል።
በዚህም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ድርድር አድርገዋል ብሏል መግለጫው።
ግንባሩም ከመንግስት የቀረበለትን ጥሪ አክብሮ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መወሰኑን መንግስት በአድናቆት ይመለከተዋልም ነው ያለው።
ከግንባሩ ጋር የተደረገው ድርድር የተሳካና ሃገራዊ መግባባት የሰፈነበት እንደነበር ያነሳው መግለጫው፥ በሰለጠነ መንገድ የሚደረግ ውይይትና ድርድርን መንግስት በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ አካላት ጋር በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
መግለጫው የግንባሩ አመራሮች በቅርብ ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ጠቅሶ፥ ቀሪ ድርድሮችም አዲስ አበባ እንደሚደረጉ ይጠበቃል ብሏል።
መንግስት ወደፊትም ህገ መንግስቱን ባከበረና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በሃገራቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመወያየትና ለመደራደር ዝግጁ መሆኑንም መግለጫው አንስቷል።