አዲስ ኣበባ፣ 4 ሚያዝያ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የመቐለ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን ይፈታል የተባለ ግድብ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ ነው።
በመቐለ ከተማ በየቀኑ 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚያስፈልግ ሲሆን፥ በዚህ ወቅት ያለው አቅርቦት ግን ከ25 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የዘለለ አይደለም።
ለዚህም በከተማው ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት የፌዴራል እና የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረጉ ቆይተዋል።
ስለሆነም የትግራይ ክልል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ባደረገው ጥረት በየቀኑ 18 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ማቅረብ የሚያስችል የገረብ መሰገን ግድብ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሁኑን የትግራይ ክልል የውሃ ሃብት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ተስፋአለም ገብረየውሃንስ ገለፁ።
የፌዴራል መንግስት ደግሞ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችል የገረብ ግባ ግድብ ለመገንባት የሚያስችል ብድር በማፈላለግ ላይ እንደነበር አንስተዋል።
በዚህም ግድቡን ለመገንባት የሚያስችል 8 ቢሊየን ብር ከቻይና መንግስት መገኘቱን ዶክተር ተስፋአለም አስታውቀዋል።
የቻይና መንግስት በብድር መልክ ሊሰጥ ፈቃደኛ የሆነው የገንዘብ መጠን በግንቦት ወር ስምምነቱ እንደሚፈረምም ጠቁመዋል።
የግድቡ ግንባታም መስከረም ወር 2011 ዓ.ም ለመጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ተስፋአለም፥ የግድቡ ግንባታ በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
ግንባታው ሲጠናቀቅም በየቀኑ 147 ሺህ ኪዩብ ሜትር ንፁህ መጠጥ ውሃ ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።