አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባውን ያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓመተ ምህረት ለስድስት ወራት ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ።
ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) መሰረት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በምክር ቤቱ ከተገኙ 490 አባላት መካከል በ395 ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ታእቅቦ አፅድቆታል።
ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ያመለክታል።
መንግስት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ፣ የአገርን ሰላምና ደህንንነት የማስከበርና የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት እውን በማድረግ የዜጎችን በነፃነት የመዘዋወር፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ መታወጁም ተጠቅሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጥስና ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተራዘመ መሄዱ ተነስቷል።
በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት የህግ ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው መንግስትን በተለያዩ መድረኮች መጠየቃቸውንም ነው መንግስት ከዚህ ቀደም የገለፀው።
በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተጋረጠውን ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አሰፈላጊ መሆኑ እንደታመነበትም አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመርማሪ ቦርድ መካከል የስድስቱ አባላት ዝርዝርም ዛሬ ቀርቦለት አጽድቆታል።
ተያያዥ መረጃዎች
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሙሉ መመሪያ
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምን ይላል?