አዲስ አበባ ፣ ጥር 25 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዳርና ዳር ሙሉ ቁመት መጠናቀቁን የግድቡ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ተናገሩ።
ኢንጂነር ስመኘው እንዳሉት አሁን ላይ የአቃፊ ግድቡ የአርማታ ሙሌት ስራ ከ11 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ሆኗል።
አሁን ላይ ያለው የግድቡ የግንባታ ደረጃም የግድቡን የሲቪል ስራ እያሳደገው ይገኛል ነው ያሉት።
በግድቡ የሃይል ማመንጫ፣ የአሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያና በግድቡ ማስተንፈሻም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኪዩብ የአርማታ ሙሌት ስራ ተከናውኗል።
ከዚህ ባለፈም ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃው የሚተኛበትና 246 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ደን ምንጣሮ ስራ እየተካሄደ መሆኑንም ኢንጅነር ስመኘው ተናግረዋል።
ግድቡ ሃይል እንዲያመነጭ የሚረዱት ተርባይኖች የሚያርፉበት ቦታ ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ማስተንፈሻ ላይ የሚገጠሙት በሮች ግንባታም በኢፌዴሪ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ አሁን ላይ በሶስት ፈረቃ ተከፍሎ 24 ሰዓት እየተከናወነ ይገኛል።