Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በመጀመሪያ ዙር የ528 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ


አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍርድ ሂደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ 528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር መቋረጡን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገለፀ።

በአራት መስፈርቶች ተለይተው ክሳቸው ከተቋረጠው ተጠርጣሪዎች መካከል 115ቱ በፌደራል ደረጃ ሲሆኑ፥ ሌሎቹ 413 ደግሞ ከደቡብ ክልል የቀረቡ ናቸው።

ከደቡብ ክልል ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች በክልሉ በጌዲኦ ዞንና በኮንሶ ወረዳ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በመሳተፍ የተጠረጠሩ ናቸው።

በፌደራልና በደቡብ ክልል ቀርበው ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች ውጭ ግን ሌሎች ክልሎች ክሳቸው የሚቋረጥላቸውን ተጠርጣሪዎች ገና አለማቅረባቸው ተመልክቷል።

የተጠርጣሪዎቹ ማንነት በቀጣይ ይፋ እንደሚሆን እና ዛሬና ነገ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ እንደሚለቀቁ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ አቃቢ ህጉ በመግለጫቸው በፀረ ሽብር ህጉ የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች የክስ መቋረጡ እንደሚመለከታቸው አንስተዋል።

በቀጣይ የፀረ ሽብርና የንግድ ህጉን ለማሻሻል የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ተመጣጣኝ ሃይል የመጠቀም ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡንም አስረድተዋል።

የተፈረደባቸው እና በይቅርታ የሚፈቱትን በተመለከተም በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት እየተለዩ መሆኑን ያነሱት አቶ ጌታቸው፥ መለየቱ ግን ጊዜ እንደሚወስድ ነው ያስታወቁት።

በመሆኑም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በተከታታይ እየተጣራ በይቅርታ እንደሚለቀቁ ገልፀዋል።

መስፈርቶቹ

በተፈፀሙ ችግሮች ሰው ያልገደለ እና ከባድ የአካል ጉዳት ያላደረሰ
ትልልቅ የኢኮኖሚ አውታሮችን ለማውደም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልነበረው
ህገመንግስታዊ ሰርዓቱን ለመናድ ቁልፍ ሚና ያልነበረው
መንግስት መስራት ሲገባው ግን ባልሰራቸው ስራዎች ምክንያት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተነድተው በግጭት እና ሁከት ውስጥ የተሳተፉ
በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያካሄደውን ግምገማ ተከትሎ አራቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት በሰጡት መግለጫ ላይ “በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ ወንጀል በመፈፀም ድርጊት ተጠርጥረው በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በምህረት ህግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ እንዲፈቱ ይደረጋል።” መባሉ ይታወሳል።