አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊቀመንበሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ላይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ “የህዝባችንና የወዳጆቻችንን ስጋት እየቀረፍን የጠላቶቻችን ከንቱ ምኞት፣ ድባቅ እየመታን ለዚሁ በቅተናል። ለውድቀት የታጨን አይደለንምና ለጊዜው ባጋጠመን ተግዳሮች ውስጥ እንኳ ብናልፍ በአሸናፊነት እንወጣለን።” ብለዋል።
“በፈፀሙት ወንጀል ምክንያት በፍርድ ቤት የተፈረደባቸው ወይም ደግሞ በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው ተይዞ በእስር የሚገኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችም የተሻለ ሃገራዊ መግባባት ለመፍጠርና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ ክሳቸው ተቋርጦ ወይም በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስነኗል::” ነው ያሉት።
በደርግ ዘመን በምርመራ ስም ልዩ የጭካኔ ተግባር ሲፈጸምበት የነበረውና በተለምዶ ማዕከላዊ በመባል የሚታወቀው የምርመራ ማእከል እንዲዘጋ ተደርጎ ሙዝየም እንዲሆን እንደተወሰነ አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።
በምትኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የሰብአዊ መብት ድርጊት መርሃ ግብር መሰረት አዲስ የምርመራ ተቋም ተቋቁሞ በሌላ ህንፃ ስራ መጀመሩም በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።
መግለጫውን የኢህአዴግ እና ደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር እና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ እና የህወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ናቸው በጋራ የሰጡት።