Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከግብጽ የአለም ባንክ ያደራድረን ጥያቄ ጀርባ


አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 19 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ብሄራዊ ስሜት አስተሳስረው የጀመሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 63 በመቶ ደርሷል።

የግድቡ ግንባታ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፥ የሁለቱ ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት ጅማሮም ኢትዮጵያውያን በተስፋ የሚጠባበቁት ጉዳይ ነው።

ከሰሞኑ ግን የግብጽ ፖለቲከኞች በግድቡ ዙሪያ እያደረጉት ያለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድና የሚያቀርቡት ሃሳብ ያልተለመደ ሆኗል።

የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ፥ ለኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በሚካሄደው አስገዳጅ ባልሆነ ውይይት ላይ አማራጭ ብለው ያቀረቡት ነጥብም የሃገሪቱን ፖለቲከኞች አካሄድ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኗል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በግድቡ ዙሪያ በሚካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት ላይ የአለም ባንክ ገለልተኛ አደራዳሪ ሆኖ ይቅረብ የሚል ሀሳብ የያዘ ረቂቅ ሀሳብ አቅርበዋል።

ይህ አዲሱ የካይሮ የዲፕሎማሲ ጅማሮ ግን እውነተኛ አወያይ ፍለጋ ወይስ ሌላ እቅድ ያዘለ እንቅስቃሴን የያዘ ነው የሚል ጥያቄን እያስነሳ ነው።

የሶስትዮሽ ብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው እንደሚሉትም፥ ግብፅ ይህን መሰል መስመሩን ያልጠበቀ ሀሳብ ስታቅርብ የመጀመሪያዋ አይደለም።

ከአሁን በፊት የአማካሪው ጥናት ገዥ እንዲሆን በሚል ሃሳብ አቅርባለች የሚሉት ሰብሳቢው፥ ይሁን እንጅ የጥናት ውጤቱ የሶስቱ ሃገራት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር አይችልም በሚል በሚል መቅረቱን አስታውሰዋል።

በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የጅኦግራፊ ትምህርት ከፍል ሃላፊ እና መምህሩ ብርሃኑ በላቸውም፥ የሃገሪቱ ፖለቲከኞች ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ እያቀረቡ ውይይቱን ለማራዘም በተደጋጋሚ እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻሉ።

በሶስቱ ብሄራዊ ኮሚቴዎች አሰራር ጥናቶቹ ተጠንተው ከተጠናቀቁ በኋላ የሶስቱ ሃገራት ባለሙያወች ሃሳቡን መቀበል አለመቀበላቸውን ለሃገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንደሚያቀርቡ፥ ከአሁን በፊት በተካሄዱ ውይይቶች የተስማማንበት ጉዳይ ነው የሚሉት ደግሞ የሶስትዮሹ ብሄራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢው ኢንጂነር ጌዲዮን ናቸው።

ሚኒስትሮቹም አአካሄዱን ከገመገሙና አዋጭ መሆኑን ከተመለከቱ በኋላ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ነጥቦች ካሉ ደረጃውን ጠብቆ ከሚኒስትሮች በላይ መታየት ባለበት አግባብ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም ነው የሚናገሩት።

ከሁለት አመት በፊት ካርቱም በተፈረመው የመርህ መግለጫ ስምምነት መሰረት የሶስቱ ሃገራት የውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት መቀመጡን ኢንጂነር ጌዲዮን ተናግረዋል።

ኢንጂነር ጌዲዮን እዛ ደረጃ ላይ ሲደረስና የሶስቱ ሃገራት ሚኒስትሮች አስፈላጊ ነው ብለው ሲመክሩም ሃገራቱ አለም አቀፍ አማካሪ መርጠው ጉዳዩን እንዲያይ እንደሚያደርጉም ነው የሚናገሩት።

በተፈረመው መርህ ስምምነት መሰረትም ጉዳዩ መጨረሻ ላይ ወደ መሪዎቹ ይሄዳልም ብለዋል ኢንጂነር ጌዲዮን፤ አሁን በግብጽ በኩል የቀረበው ሃሳብ ግን ሊመከርበት የሚገባ መሆኑን በመጥቀስ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጣቢያችን ያነጋገራቸው ምሁራንም የግብጽ ፖለቲከኞች ጊዜያዊ ጥቅምና በህዝባቸው ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ውይይቱን ለማራዘም ታሳቢ ያደረገ አካሄድ እየተከተሉ ነው ይላሉ።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ፖለቲካ ሳይንስና ስትራቴጂክ ጥናት ክፍል ባልደረባ መረሳ ፀሃዬ የአለም ባንከ አደራዳሪ ሆኖ የመቅረብን ገለልተኝነት በጥያቄ ይመለከቱታል።

ባንኩ ከአመሰራረቱም አስተዋጽኦ ላደረጉ ሃገራት ባደላ መልኩ ድምጽ የሚሰጥ በመሆኑ በራሱ ገለልተኛ ሆኖ አያውቅም ብለዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲው ብርሃኑ በላቸውም ግብጽ አለም ባንክን አሸማጋይ ማድረጓ፥ አንድም በተቋሙ ሊኖሩ የሚችሉ ግብጻውያን ባለሙያዎችን ለመጠቀም

አልያም ደግሞ ኢትዮጵያ የባንኩን አደራዳሪነት በምትቃወምበት ወቅት ከባንኩ ጋር ያላትን ግንኙነት ያልተፈለገ ገጽታ ለመስጠት ከማሰብ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና በአሜሪካው ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ክፍል ባልደረባው አባይ ይመር ደግሞ፥ ግብጽ ይህን ሃሳብ ያቀረበችው ግድቡ በራሱ የጎላ ተፅዕኖ ያሳድርብኛል ብላ ሳይሆን የሱዳን ቀጣይ ተጠቃሚነት ላይ ስጋት ስላላት ነው ይላሉ።

ምክንያቱም ሱዳን በመስኖ ሊለማ የሚችለውን ሰፊ ሜዳማ ቦታዋን ውሃው ባለው ሃይል ሳቢያ መገደብና በሚፈለገው ልክ ማልማት አትችልም፥ ኢትዮጵያ አባይን ስትገድብ ግን ወንዙ ሱዳን ላይ ተረጋግቶ የሚያልፍ በመሆኑ ሱዳን የመስኖ ልማቷን ማካሄድ ያስችላታል ነው የሚሉት።

ከዚህ አንጻርም ከሚጠበቀው በላይ ውሃ ሱዳን ልትጠቀም ስለምትችል ወደ ግብጽ የሚሄደው የውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ስጋት ላይ እንደጣላትም አስረድተዋል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ በግብጽ ላይ አንዳች ጉልህ ተፅዕኖ እንደማይኖረው በግልጽ እየታወቀ ፖለቲከኞቿ ጉዳዩን ለተሰሚነት መነገጃ እያደረጉት ስለመሆኑም ያነሳሉ።

የሃገሪቱ ፖለቲከኞች አካሄድም ኢትዮጵያን እንደ ስጋት በመሳልና በማስረዳት የግብጻውያንን ሃሳብ ከማስቀየር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ገልጸዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ እና የስትራቴጂክ ጥናት ክፍል ባልደረባው መረሳ ፀሃዬም፥ ግብጾች አዲስ አበባ ላይ ይህን መሰል ሃሳብ ማቅረባቸው ሱዳንን አስኮርፎ ከቀጠናው ዲፕሎማሲ ጉዞዋ ማስወጣት እና ከኢትዮጵያ ጋር ማለያየት መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብጾች የኢትዮጵያውያንን የሃይማኖትና ብሄር ስብጥርን እንደ ክፍተት ለመጠቀም በየጊዜው መሞከራቸውን የሚያነሱት ብርሃኑ በላቸው፥ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን አቻችለው ለግድቡ ያላቸውን ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በትብብር የመስራት መንፈሷን አጠናክራ እንደምትቀጥልና ከዚህ መርህ ባፈነገጠ መልኩ የሚካሄድ አፍራሽ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለውና የተፈጥሮ ሀብቷን

ለመጠቀም የማንንም ይሁንታ የማትጠብቅ መሆኑን ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ ስትገልፅ መቆየቷም ይታወሳል።