Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሕዝቦችን ጥያቄ በተሟላ መልኩ የሚመልሱ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው አመት በድርጅቱ የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ አፈፃፀም በዝርዝር መገምገም መጀመሩን አስታውቋል።

ኮሚቴው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ቀደም ሲል የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የነበሩና የተተኩ ነባር ታጋዮችን ባከተተ አግባብ ግምገማው እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

ኢሕአዴግ የህብረተሰቡን ለውጥ የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ አስተማማኝ የለውጥ መሪ የሚሆነውም ራሱንም እየለወጠ መሆኑን በፅኑ ያምናል ያለው መግለጫው፥ ሁልጊዜም ራሱን እየገመገመ ከነባራዊው ሁኔታ አንጻር የሚመጥን ድርጅታዊ ቁመና ለመያዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ በፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት አቅጣጫ ወደፊት እየገሰገሰች እንደምትገኝ መላ የሃገራችን ሕዝቦችና አለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር በገሃድ የመሰከሩት ሃቅ መሆኑንም ነው ያነሳው።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በመታየት ላይ የሚገኙት በዋነኛነት ከልማት፣ ከመልካም አስተዳደርና ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮች የማያዳግምና መሰረታዊ የሆነ መፍትሄ እንደሚሰጥ ያነሳው መግለጫው፥ እስካሁን በተደረጉት ግምገማዎችም የችግሮቹን አይነተኛ ባህሪዎችና ዋነኛ መንስዔዎች አስመልክቶ ዝርዝር ውይይት መደረጉን፤ በአመራሩ ዘንድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኃን የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር መቻሉንም በመግለጫው አንስቷል።

የአስተሳሰብ አንድነት ለተግባር አንድነት መሰረት በመሆኑም ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰጡትን ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደወትሮው በላቀ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በፈጠረው ተስፋና የተከመሩ ፖለቲካዊ ችግሮች ከፊት በደቀኑት ስጋት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንዳለ በትክክል ይገነዘባልም ብሏል።

ኮሚቴው የተጀመረውን ፈጣን እድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እስካሁን የመጣበትን ርቀት ለማሳካትም ሆነ ወደፊትም ለማስቀጠል፥ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ከአሁን በፊት የነበረው አኩሪ በመተጋገል ላይ የተመሰረተ አንድነት በቦታው ላይ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

እስካሁን ባደረገው ግምገማ በአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የእርስ በርስ መጠራጠር ያመዘነበት፣ አለመተማመን ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣበት መሆኑን በጥብቅ እንደተገነዘበ ኮሚቴው በመግለጫው አስታውቋል።

በመሆኑም በዚህ ላይ ተመስርቶ በተደረገው ሰፊና ጥልቅ ውይይት በዚህ ረገድ የታዩ ችግሮችን በስፋት መርምሮ የቆየውን የሃሳብና የተግባር አንድነት ለማምጣት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረሱን አመልክቷል።

ስራ አስፈፃሚው በተጨማሪም ባለፉት ሁለት አመታት ኢሕአዴግ ያደረገው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካታ አበረታች ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም፥ በሚፈለገው ደረጃ ጥልቀት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተመልሶ ወደ አዘቅቱ መመለሱን በትክክል ማስቀመጡን ነው የገለፀው።

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በዋነኛነት የድርጅቱ አመራር ያሳየው ድክመት የፈጠራቸው መሆናቸውን በሚገባ ይገነዘባል ያለው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ሃገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ለምትገኝበት አስጊ ሁኔታ ድክመቱ ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብሏል።

የድርጅቱ በየደረጃው ያለው አመራር ከሞላ ጎደል የዚሁ ድክመት ተጋሪ ቢሆንም ስራ አስፈፃሚው የዚህ ችግር ዋነኛ ባለቤት መሆኑንና ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እየተሸረሸረ ችግሮችን በቁጭት መንፈስ ከመፍታት ይልቅ የእርስ በርስ ንትርክ ላይ እንደሚያተኩር መግባባት ላይ መደረሱንም አመልክቷል።

የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ በድርጅቱ ውስጥ ያለበት ደረጃ ከፍተኛ ድክመት የሚስተዋልበት መሆኑንና ህብረተሰቡ ውስጥ ጤናማ ዴሞክራሲያዊ ሕይወት በመፍጠር ረገድ ያደረሰውን ተፅዕኖ ስራ አስፈፃሚው በሚገባ እንደሚረዳም አስታውቋል።

እስካሁን በተደረገው ጥልቅ ግምገማ ከስኬት ጎዳና እያራቁ የሚገኙ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መታጣት፣ የእርስ በርስ መጠራጠር፣ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ እጦትና የሕዝባዊ ወገንተኝነት መሸርሸር ተገቢ ውይይት ተደርጎባቸው የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ፣ የልማትና የሰላም ጥያቄዎችን በሚገባ ለመመለስ በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቋል።

ከምንም ነገር በላይ በሃገሪቱ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶችን ከመፍታትና የፌዴራል ስርዓቱን ከአደጋ ከመታደግ አንፃር የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ባረጋገጠ መልኩ የተጠናከረ ስራ መስራት እንደሚገባ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የጋራ አቋም ይዣለሁ ብሏል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ግምገማውን ለሃገሪቱ ሕዝቦች ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስና ለፌዴራል ስርዓቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ አስፈላጊ የሆኑ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥና ለዚህ ግብ ዝግጅት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችለውን የተሳካ ውይይትና መተጋገል በፅናት ቀጥሎበት በቅርብ ጊዜ በድል እንደሚጠናቀቅ አስታውቋል።

ሂደቱንም ለመላው የሀገሪቱ ሕዝቦችና ለኢሕአዴግ አባላት በተከታታይ እንደሚገልፅም አስታውቋል።