Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ተከበረ


አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በደማቅ ስነ ስርዓት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከበሮ ተጠናቀቀ።

የኢሬቻ በዓል በአመት ሁለት ጊዜ ከክረምት መግባት በፊት እና ክረምት ከወጣ በኋላ የሚከበር ሲሆን፥ የመጀመሪያው በተራራማ ስፍራ ለምስጋናና ቀጣይ ወራትን ብሩህና ስኬታማ ለማድረግ የሚከበር ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በሃይቅ እና ወንዞች አካባቢ ምስጋና ለማቅረብና ስኬትን ለመሻት ይከበራል።

በዓሉ የኦሮሞ ህዝብ የዝናብ፣ የጎርፍ እና የጨለማን ወቅት አሻግሮ ለፀደዩ ብርሃን ላደረሰው ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

የመስቀል በዓል ባለፈ በመጀመሪያው እሁድ ለፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል፥ በተለያዩ ቦታዎች የሚከናወን ቢሆንም በዋነኝነት በቢሾፍቱ በሆራ አርሰዲ ሀይቅ ላይ የሚካሄደው የበዓል አከባበር ግን ታላቅ ቦታ የሚስጠው ነው።

በበዓሉ ጥቅም ላይ የሚውለው ቄጤማ እርጥብ ሳር በኦሮሞ ባህል ለምለም ህይወትን የሚያሳይ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠው ነው።

በበዓሉ ላይ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ከመላው ሀገሪቱ ብሎም በርካታ የውጭ አገራት ዜጎች ተሳትፈዋል።

ስነ ስረዓቱ በአባ መልካ ምርቃት የተከፈተ ሲሆን፥ በመቀጠል አባ ገዳዎች መርቀው የኢሬፈና ስነ ስርዓት ተካሂዶ ተጠናቋል።

በአሁኑ ወቅት በበዓሉ ላይ የተገኙ ታዳሚዎች ፈጣሪያቸውን አመስግነው ወደመጡበት ተመልሰዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫም በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ገልጿል።