Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ለሆቴሎች፣ ሪል እስቴቶችና ግዙፍ ሞሎች መሬት በምደባ መስጠት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው


አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 14 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ያለው የመሬት አቅርቦት ችግር አለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎችን በብዛት ለማልማት ችግር እየፈጠረ ነው ተባለ።

አዲስ አበባ በ2016 አለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎቿ 12 ደርሰው እንግዶቻቸውን የሚያስተናግዱበት 2 ሺህ 58 መኝታ ያላቸው ሆነዋል።

ይሁን እንጅ በአፍሪካ የሆቴል ኢንቨስትመንትን በማስፋፋትና በመኝታ ቤት ቁጥር ብዛት ረገድ 8ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ይህ አሃዝ እንደ ከተማዋ የአለም የዲፕሎማሲ ከተማነት ደረጃን ካላገኙ የአፍሪካ ከተሞች አንጻር ሲወዳደርም አነስተኛ ነው።

ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ ሀገር በሚቀጥሉት አራት አመታት አለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው እና 58 ሺህ የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ሆቴሎች እንዲኖራት እቅድ ይዛለች።

ይህን እቅድ በአፍሪካ መዲና እውን ለማድረግ ግን በአዲስ አበባ ከአምስት ኮከብ ሆቴል በላይ ለሚገነቡ ባለሀብቶች መሬት ማግኘት ከባድ መሆኑ ለባለሀብቶች የራስ ምታት ሆኖባቸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ እንደሚሉት፥ በአዲስ አበባ አዳዲስ ሆቴሎች አለመገንባታቸው መዲናዋን በአለም ውዱ የመኝታ ክፍያ የሚጠየቅባት ከተማ እንድትሆን አድርጓታል።

በሆቴል ዘርፍ ላይ በጥምር ጥናት ያደረጉት አቶ ኢብሳ ጎበና እና አቶ አንዱአለም ጉደታ በፈረንጆቹ 2013 የሆቴል ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ በሚል በሰሩት ጥናት፥ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሆቴል አገልግሎት ፍላጎት ቢኖርም አቅርቦቱ ግን እጅግ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአንጻሩ ሃገሪቱ ከቱሪዝም ዘርፍ የምታገኘው ገቢ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሲሆን፥ ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የስራ እድል ፈጠራ የ8 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ አለው።

ሆቴል እና ቱሪዝም ተመጋጋቢ ሆነው የሚያድጉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ቢሆኑም፥ የሆቴል ዘርፉ እድገት በሚጠበቀው ልክ አልሆነም፤ ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉን ያነሳሉ ኮሚሽነር ፍጹም።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክ እና ማስተላለፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አልዬ በበኩላቸው፥ በከተማዋ በ2009 ዓ.ም በርካታ የሆቴል መስሪያ ቦታ ፍቃድ ጥያቄ መቅረቡን ይናገራሉ።

የከተማ አስተዳደሩ በሊዝ አዋጅ 721/2004 መሰረት፥ መሬትን ለሆቴሎች፣ ሪል እስቴት እና ግዙፍ ሞሎች የሚያስተላልፈው በጨረታ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጀማል፥ ይህ መሆኑ ሆቴል መስራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች መሬት የማግኘት እድላቸውን አጥብቦታል ይላሉ።

አሁን ላይም ለሆቴሎች፣ ሪል እስተቴቶችና ግዙፍ ሞሎች መሬት ከጨረታ ይልቅ በምደባ እንዲሰጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ በስራ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል ሀገሪቱ በቀጣይ አራት አመታት በሆቴል ልማት ለመድረስ ያቀደችውን ግብ ማሳካት የሚያስችላት ይሆናል ብለዋል።