Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ግንቦት 20 በእኩል የመልማት፣ የህግ የበላይነትን በማስፈን የኢትዮጵያ ህዳሴ ፍኖተ-ካርታ የተቀረፀበት ዕለት ነው-ጠ/ሚ ሃይለማርያም


አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ግንቦት 20 በእኩል የመልማት፣ የህግ የበላይነትን በማስፈን የኢትዮጵያ ህዳሴ ፍኖተ-ካርታ የተቀረፀበት ዕለት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡

የግንቦት 20 ቀን 26ኛ ዓመት የድል በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሊኒየም አዳራሽ በተከበረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያ ህዝቦች በታሪካችን አዲስ ምእራፍ ለተጀመረበት የድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

የድል ቀኑ የጭቆና እና የአፈና ስርዓትን በማስወገድ በምትኩም በመከባበርና በመፈቃቀድ የተመሰረተ ፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ ስርኣትን በመገንባት፥ በረጅሙ የጭቆና ታረካችን አዲስ ታሪክ የጻፍንበት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የሰፈነበት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገቶችን በማፋጠን ሃይማታዊና ጾታዊ እኩልነት የተረጋገጠበት እና ህገመንግስታዊ ዋስትና የተገኘበት እለት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ድሉ ባለፈው ስርዓት የነበረውን የሰላም ችግር ስር ነቀል በሆነ መንገድ በመፍታት ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ አስችሏል፡፡

የሰላም መረጋገጡም ላለፉት ዓመታት የማምረት አቅምን በመጨመር፥ ከማሽቆልቆል ጉዞ በመውጣት የልማት ውጤት ትሩፋት ተቋዳሽ አድርጓል ነው ያሉት አቶ ሃይለማርያም፡፡

በሀገሪቱ በየደረጃው የተመዘገበው የልማት ውጤትም የበርካቶችን ሕይወት በሁሉም መስኩ የተቀየረ ሲሆን፥ ይህም ሀገሪቱ በዓለም ላይ ያላትን ተቀባይነት ማሳደጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡

ይህ የሆነው ሁሉም ዜጋ ሀገሪቱ ባስመዘገበቺው እድገት ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡

የግንቦት 20 ድል የራሳችንን ሰላም ለማረጋገጥና ባልተረጋጋ አካባቢ ሰላማዊት ሀገር በመፍጠር ለጎረቤት ሀገራት የሰላም አጋር መሆን ማስቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ሀገሪቱ በምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ውጤት በማስመዝገብ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ መሆኗም የግንቦት 20 ትሩፋት ነው ብለዋል፡፡

ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያቀፈውን ህገ መንግስት ተግባራዊ በማድረግ ረጅምና ውጤታማ ጉዞን መጓዝ ማስቻሉን ነው ያብራሩት፡፡

በዴሞክራሲዊ ምርጫ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበት ሀገርና የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱም አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

በድህረ ግንቦት 20 የተመዘገበው ስኬት መንገድ ግን ጉዞው አልጋ በአልጋ እንዳልነበረ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአንድ በኩል ልማታዊና ዴሞክራሲዊ በሌላ በኩል ከሀገሪቱ እድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርም የተስተዋለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ማዕዘናት በአንዳንድ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይሎች የኪራይ ሰብሳቢነትን፣ የትምክህትና የጥበት አስተሳሰቦችን ወደ ህዝቡ ለማሰራጨት በመሞከር፥ ስርዓቱን አድልኦ ያለበት በማስመሰል በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን ለመፍጠር የተሞከረበት እንደነበርም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም በንቃት በመታገል ልማታዊነትን በማስፈን የድህነት ጠበቃ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን፥ ህዝቡ በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎችን እንዲሁም የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነትን በማፋጠን፥ የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል መሪው ድርጅት ኢህአዴግ እና መንግስት በሙሉ ሃይላቸው እየተጉ በመሆኑ ህዝቡ ከጎን እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

የግንቦት 20 ቀን 26ኛ ዓመት የድል በዓል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እና በተለያዩ ሀገራት ተከብሯል፡፡