Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ተግባራት የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ


አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት ለሚያከናውናቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አደረገ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂቫ ጋር ተወያይተዋል።

ዳይሬክተሯ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ ከዓለም ባንክ ጋር በቀጣይ ሦስት ዓመታት በአጋርነት ለምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች የሚውል የ4 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ለተፋሰስ ልማት፣ ለሴቶች ሥራ ፈጠራና ለሴፍቲኔት ፕሮግራም እንደሚውልም ገልጸዋል።

በድህነት ቅነሳና በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰራውን ሥራ አድንቀው በአገሪቷ ያለውን እምቅ የፈጠራ አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በተለይም በሴፍትኔት ፕሮግራም እየተከናወነ ያለው ተግባር ዜጎች ከድርቅ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በዘላቂነት እንዲቀየርና እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉ የሚደነቅ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በቀጣይም የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በጋራ ለመከወን ምክክር እየተደረገ መሆኑንና መግባባት ላይ ሲደረስ የድጋፉ መጠን ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው አገሪቷ ድህንትን ለማሸነፍና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት፣ ከዓለም ባንክ ጋር መስራቷ ለውጥ ማምጣቱንና ድጋፉ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ባንኩ ለኢትዮጵያ በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በስራ ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲሁም በሴፍትኔት ፕሮግራም የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።