Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም በሶማሊያ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ለንደን አቀኑ


አዲስ አበባ ግንቦት 1/2009 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለንደን በሚካሄደው በ”2017 ሶማሊያ ጉባዔ” ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ወደ ስፍራው አቅንተዋል።

“የ2017 ሶማሊያ ጉባዔ” አገሪቷ ላለፉት አምስት ዓመት ያስመዘገበችውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚያስችል ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

ጉባኤው የምስራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች እና ሌሎች ዋነኛ አጋር አካላትን በጋራ ያገናኛል::

በሶማሊያ እየታየ የመጣውን የሰላምና ደህንነት ለውጥ በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ባተኮሩ ጉዳዮች ላይ ይመክራል።

በ2020 የአገሪቷን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ዓለማቀፋዊ የአጋርነት ስምምነቶች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባኤው በሶማሊያ የፌዴራሉና የአባል መንግስታቱ በጋራ በሚስማሙባቸው ጉዳዮች ላይም ትኩረት ይሰጣል።

በአገሪቷ የሴት ወታደሮችን የወደፊት ሁኔታ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶች ሳይጣሱ ሽብርተኝነትን መዋጋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ውይይት ይካሄዳል።

እ.ኤ.አ 2011 ሶማሊያ ካለመረጋጋቷም በላይ አብዛኛው የአገሪቷ ክፍል በአል ሽባብ ቁጥጥር ስር ነበር። በአገሪቷ በተከሰተው ረሃብም ወደ 250 ሺ የሚጠጉ ዜጎቿ ተቀጥፈዋል:: በአገሪቷ የባህር ላይ ውንብድና በሰፊው ከመንሰራፋቱ የተነሳ በተመሳሳይ ዓመት ብቻ በዓለማቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሰባት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኪሳራ አድርሷል።

ይህን ተከትሎ ለንደን በ2012 ሶማሊያን የተመለከተ የመጀመሪያውን ዓለምአቀፍ ጉባዔ ያካሄደች ሲሆን፤ ከጉባኤው ማግስት ጀምሮ የሶማሊያ ሰላም መሻሻል ጀምሯል።

እኤአ በ2012 በሶማሊያ የፌዴራል መንግስት ስርዓት ማዋቀር ተችሏል። በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም አሰከባሪ ሃይልም በአገሪቷ ሰላም ከማስፈን ባለፈ አልሸባብን ዋና ዋና ከሚባሉ ከተሞች ለማስለቀቅ ችሏል::

ሶማሊያ በ2017 የተሳካ ምርጫ በማካሄድ የአገሪቷን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ አብዱላሂ መሃመድ በፕሬዚዳንትነት ወደ ስልጣን አምጥታለች።

በሶማሊያ በየጊዜው የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማሰቆም እና በድንበሮች አካባቢ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን በአገሪቷ ያለውን ደህንነት ማሻሻል ወሳኝ በመሆኑ ጉባኤው ይህንን ለውጥ ለማፋጠን በሚያስችሉ ዘዴዎቸ ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።