Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ባለስልጣኑ ከ28 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ መድኃኒት አስወገደ


አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከ28 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት እንዲወገድ ማድረጉን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ የሶስተኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃጸም ግምገማ ትናንት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በባለስልጣኑ የፕሮጀከት ዝግጅትና ማስተባበሪያ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ልሳነወርቅ ዓለሙ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት፥ የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈና ህገወጥ የሆነ መድኃኒት እንዲወገድ የተደረገው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ነው።

የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መደኃኒቶች የተያዙት በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻና በመደበኛ የቁጥጥር ስራዎች መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ባለስልጣኑ ከአለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በቶጎ ውጫሌ፣ ሞያሌ፣ ቃሊቲ፣ መተማና በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ድንገተኛ ፍተሻ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ውጤታማነት ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴም በ129 የታሸጉ ጭማቂዎች ናሙናዎች ላይ በተካሄደው የላብራቶሪ ምርመራ 20ዎቹ መስፈርቱን ሳያሟሉ በመቅረታቸው ምርቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ተደርጓል ብለዋል።

ለድህረ ገበያ ጥናት የተሰበሰቡ 215 የማንጎ ጭማቂ ናሙናዎች የጥራት ምርመራ የተሰራላቸው ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 103 ናሙናዎች መስፈርቱን ሳያሟሉ ቀርተዋል፡፡

ከ28 የጨቅላ ህጻናት ወተት ናሙናዎች ውስጥ 22ቱ መስፈርቱን ባለማሟላታቸው ከ94 የዘይት ናሙናዎች ውስጥ ደግሞ 19ኙ መስፈርቱን ሳያሟሉ በመቅረታቸው እንዲወገዱ መደረጉንም አስተባባሪው አመልክተዋል።

በተለይ ባለ 20 ሊትር 7 ሺህ 500 ጀሪካን ዘይት የአምራች ስምና አገር “ባች ቁጥር ” የተመረተበት ጊዜና መጠቀሚያ ጊዜ እንዲሁም የምርቱ ይዘት ስለማይገልፅ ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ተደርጓል።

የጥራት መስፈርትን አሟልተው ያልተገኙ መድሀኒቶችና የኮንዶም ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ እና ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ የማድረግ ስራ መከናወኑንም ነው አቶ ልሳነወርቅ ያብራሩት።

በሌላ በኩል በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ ቁጥጥርና ፍተሻ በማድረግ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሣርያዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የምግብና መድኃኒት ንግድ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያም በ182 የምግብ አምራቾች ላይ በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ፣ በጨው አምራቾችና አከፋፋዮች በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ጥናት ተደርጎበታል፡፡

የጥናቱ ውጤቱ ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ አሰፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ በበኩላቸው፥ ባለስልጣኑ በጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የቁጥጥር ዘርፉን ለማጠናከር አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመቀየስ ሁሉንም የልማት ኃይሎች ለማስተባበርና ለማንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የጤና ቁጥጥር ስራ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ከህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ እቅድ በማውጣት ለውጤታማነቱ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት።

ባለስልጣኑ ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው የስራ አፈፃጸም ግምገማ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የሕዝብ ክንፍና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።