አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተገነቡ ያሉት የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፓርኮች አርሶ አደሮችን ከምንም ደረጃ ተነስተው ወደ ትርፍ አምራችነት ለመሸጋገራቸው ማሳያ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ የይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይን ባስቀመጡበት ወቅት ነው።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ የአከባቢው አርሶ አደሮች የሚያመርቷቸውን እና በዓለም ታዋቂ የሆኑትን የሲዳማ ይርጋ ጨፌ እና ጭሬ አካባ የቡና ምርቶችን አቀነባብሮ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር መብራህቱ መለስ እንዳሉት፥ ፓርኩ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባ ሲሆን፥
በቅድሚያ የሚለማው 215 ሄክታር መሬቱ ነው።
ይህን ለማልማት የሚያስችል ዝርዝር የዲዛይን ጥናትም ተዘጋጅቷል ነው ያሉት ዶክተር መብራህቱ።
ፓርኩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚቋቋሙበት፣ ፋብሪካዎችን የሚመግቡ በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ዙሪያ የሚገነቡ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት እና የአርሶ አደሩን ምርቶች የሚሰብስቡ ማዕከላትን ያካተቱ ሶስት ዋና ዋና ክፍሎች ይኖሩታል።
በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ጥናትን መሰረት ያደረጉ የጥሬ እቃ መጋዘኖች፣ ቤተ ሙከራዎች እና የአንድ መስኮት አገልግት መስጫዎች ክፍሎችም እንደሚገነቡለት ተጠቁሟል።
በውስጡ 60 ትላልቅ እና 120 መካከለኛ የተለያዩ ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ።
ፓርኩ ሙሉ ሥራውን ሲጀምርም ለ166 ሺህ ሰዎች በቀጥታ እንዲሁም ለ133 ሺህ ሰዎች በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ፥ የፓርኩ መገንባት ለጌዲዮ እና ሲዳማ ቡና አምራቾች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ባለሃብቶች በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኩ እንዲሰማሩ ክልሉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት አቶ ደሴ።
ለግንባታው 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን፥ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥም ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከፓርኩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስድስት የተለያዩ ማዕከላት ሶስቱ በሲዳማ ዞን፣ ሶስቱ ደግሞ በጌዲኦ ዞን እንደሚቋቋሙ ተመልክቷል።