Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በኦሮሚያ የሚገኙ ግዙፍ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን የክልሉ ወጣቶች እንዲያከፋፍሉ ተስማሙ

በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ሐሳብ መሠረት፣ የሲሚንቶ ምርቶቻቸውን የተደራጁ የክልሉ ወጣቶች እንዲያከፋፍሉላቸው መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

ሪፖርተር ከክልሉ መንግሥት ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማጠናከር በክልሉ ከሚገኙት ካፒታል ሲሚንቶ፣ ዳንጎቴ ሲሚንቶና ሚድሮክ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጋር በመወያየት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በስምምነቱ መሠረት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ለምርታቸው የሚያስፈልጉዋቸውን ግብዓቶች ከወጣቶች ገዝተው እንዲጠቀሙ፣ የክልሉ ወጣቶች በቅናሽ ዋጋ የሲሚንቶ ምርት ተረክበው በማከፋፈል ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ፋብሪካዎቹም በኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ወጣቶች የአቅም ግንባታ ለመስጠት መስማማታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ የስምምነቱ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ ለወጣቶቹ ሥልጠናና ድጋፍ ካልተደረገላቸው ግን በገበያ ሰንሰለታቸው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሒልተን በተካሄደ የሲሚንቶ ጉባዔ ላይ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በባለሀብቶች ተይዘው ነገር ግን መልማት ያልቻሉ የማዕድን ይዞታዎችን በመንጠቅ ለክልሉ ወጣቶች የማስተላለፍ ሥራ ተጀምሯል፡፡

በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሸዋ ዞን ግምቢቹ፣ ቦስት፣ ዱግዳ፣ አዳማ፣ ሉሜ፣ ፈንታሌና ቦረና ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት 615 ወጣቶች በማዕድን ዘርፍ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስተሮችን እያባረረ ነው ተብሎ የሚነዛው ወሬ መሠረተ ቢስ መሆኑን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ‹‹የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት›› ይፋ ማድረጉን ባለፈው ዕትም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
Source: Reporter