Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማያቀርቡ አምራቾች ላይ ቅጣትን ተፈጻሚ ሊያደርግ ነው


አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአሁን በሁዋላ ውላቸውን አክብረው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማያቀርቡ አምራቾች ላይ ቅጣትን ተፈጻሚ አደርጋለሁ ብሏል ።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው ለውጭ ገበያ ምርት እናቀርባለን ቢሉም፥ ቃላቸውን በማጠፍ ለሀገር ውስጥ ገበያ ምርታቸውን የሚሸጡ ባለሀብቶች በወጭ ንግድ የሚፈለገውን ያክል ገቢ እንዳይገኝ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

ችግሩ ምርት ለውጭ ገበያ ሸጠን የውጭ ምንዛሬ እናመጣለን በሚል የመንግስትን ማበረታቻ በሚያገኙ ባለሀብቶችም የሚታይ ሲሆን፥ ይህ የሆነው በመንግስት በኩል የሚደረገው ቁጥጥር በሚፈለገው ደረጃ ስላልሆነ መሆኑም ይነገራል ።

ባለፉት አምስት ወራት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ አፈፃፀምን በሚመለከት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የዘጠኝ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ዘርፎች ከገቢ አንፃር ያላቸው አፈፃፀም በአማካኝ 59 በመቶ ነው።

ላለፉት አራት ዓመታት እምብዛም ለውጥ አላመጣም በሚባለው የአምራች ኢንዱስትሪውና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ አነስተኛ መሆን፥ የአምራቾች አቅም ማነስ፣ የምርቶች በአይነትም በብዛትም ማነስና የአለም አቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ ተጠቃሽ ናቸው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አሰፋ ተስፋዬ፥ በሃገር ውስጥ ለወጪ ንግድ ዓላማ ወደ ስራ ገብተው ስራ የጀመሩ አምራቾች ምርቶቻቸውን ወደ ውጪ ሳይልኩ ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸው ሃገሪቱ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዳታገኝ ማድረጉን ገልጸዋል።

ችግሩ በሃገር አቀፍ ደረጃ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር በመንግስት በኩልም ተገቢው ትኩረት ተነፍጎታል ያት ደግ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽነሩ ዶ/ር ይናገር ደሴ ናቸው።

ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች ከስጋና ወተት፣ ከምግብና መጠጥ እንዲሁም ከሌሎች አምስት ዋና ዋና የወጪ ንግድ ዘርፎች ባለፉት አምስት ወራት 279 ሺህ ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም፥ የተገኘው ገቢ 167 ሺህ ዶላር መረጃዎች ያሳያሉ።

ለውጪ ንግድ ፈቃድ ወስደው ምርቶቻቸውን ግን በሃገር ውስጥ የሚያቀርቡ አምራቾችን ለመቆጣጠር ከማስጠንቀቂያ የዘለለ እርምጃ አለመወሰዱን ነው የተናገሩት አቶ አሰፋ።

የአምራች ኢንዱስተሪውን ዘርፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት መንግስት የተለያዩ ማበረታቻዎችን የሚጥሰጥ ሲሆን፥ የአሰራር ውላቸውን ጥሰው የተገኙት አምራቾች ላይ የምርት ፈቃድን እስከመንጠቅ የደረሰ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽነሩ ዶክተር ይናገር ደሴ እንደተናገሩት ውጤትን መሰረት ያደረገ የማበረታቻ ስርዓትን መዘርጋትም ሌላው በመንግስት በኩል የአምራች ዘርፉን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ የሚወሰድ መፍትሔ ነው፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የኤክስፖርት ገቢን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ወደ 25 በመቶ ከፍ በማድረግ ከዘርፉ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።

በዘርፉ የሚታየውን ከውል የወጣ አሰራርንና በማበረታቻ መልክ የሚሰጠውን የሃገር ሃብት ከብክነት ለመታደግ በዘርፉ ላይ የቁጥጥር አሰራሩን ለማጥበቅ መዘጋጀቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠቁሟል።