Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

በዓሉ ሃገራዊ አንድነታችንን እና ልማታችንን ለማፋጠን ለህዝባችን ቃል የምንገባበት ነው – የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ


አዲስ አበባ ፣ የካቲት 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው 42ኛ አመት የህወሃት የምስረታ በዓል የተጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞን በማጠናከር ሃገራዊ አንድነታችንን እና ልማታችንን ለማፋጠን ለህዝባችን ቃል የምንገባበት ነው ብሏል የድርጀቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ።

በቀደመው ዘመን በሰላም ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ እንደነበር ከአመታት በፊት የችግሩ ሰለባ የነበሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ሰዎች በየቦታው እንደሚገደሉና ንብረቶች እንደሚወድሙም ነው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውሱ ነዋሪዎች የሚናገሩት።

በመላ ሀገሪቱ ሁሉም ዜጎች በአንድ ድምፅ ስለፖለቲካ ማውራት የጀመሩበት ወቅትም ነበር።

በወቅቱ የነበረው የህዝቡ ስቃይና ምላሽ ያጣ ጥያቄን ያነገቡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነበሩ ሰባት የህወሃት መስራቾችም ይህን ብሶት የሞራል ስንቅ በማድረግ ደደቢት በረሃ ገቡ።

ከመስራቾቹ አንዱ የሆኑት አቶ አባይ ፀሃዬ እነዚያ የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት በትግል ብቻ በመሆኑ ይኸው መተግበሩን ይናገራሉ።

በረሃ የወረዱት ወጣቶቹ በርካታ የእነሱን ሃሳብ የሚቀበሉ እና ለመተግበር የቆረጡ ወጣቶችን በመጨመርም ቁጥራቸውን ከፍ አድርገዋል።

በፅናት እና በአላማም በርካቶች አልፈዋል፤ የኢትዮጵያ ህዝቦችም በዚህ ጥላ ስር ተጠልለው መራራውን ትግል በድል ተወጥተዋል።

ከዚያ ወዲህም የህዝቦች የማንነት ጥያቄ፣ በቋንቋ የመናገር እና የመልማት ጥያቄም ተመልሷል።

ወጣቶቹ የተነሱበት አላማም በአንድነታቸው ሰምሯል፤ ልፋታቸውም ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ውጤት አፍርቷል።

የልማት እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መልስ እያገኙ ቢመጡም፥ ከፍተኛ አመራሩ ህብረተሰቡን ያረኩ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ እንደሚገባው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የትጥቅ ትግሉ መሰረት የሆነውና ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የተመሰረተበት የካቲት 11 ደግሞ ከነገ በስቲያ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

ይህን አስመልክቶ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በላከልን መግለጫ፥ ህወሃት ባለፉት አመታት በክልሉ በየዘርፉ ለውጦች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን አስታውሷል።

በከተሞች ግብርና መር የሆነው የሃገሪቱ ፖሊሲ የክልሉ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ከማድረግ ባለፈ ጥሪት እንዲቋጥሩ እያስቻለ መሆኑንም ነው ማዕከላዊ ኮሚቴው ያስታወሰው።

በከተሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ሀብት ማፍራት መጀመራቸውን የጠቀሰው መግለጫው፥ ከተሞች የኢንቨስትመንት ምንጭ እና ለኢንዱስትሪ መደላድል መሆን መጀመራቸውንም ይገልጻል።

ዴሞክራሲን ከማረጋገጥ አንፃርም የክልሉን ብሎም የኢትዮጵያ ህዝቦች ማንነታቸው ተከብሮላቸው እና በቋንቋቸው መናገር እና መማር እንዲሁም ባህላቸውን ማክበር ጀምረዋል ብሏል ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው።

ሆኖም ግን አሁንም በሀገሪቱ እየተፈጠረ ካለው ሃብት እና እድገት አንፃር በርካታ ተግዳሮቶችም አብረው መምጣታቸውን ይጠቅሳል መግለጫው።

እነዚህን ተግዳሮቶች ደግሞ ህወሃት ኢህአዴግ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት በጥልቀት በመታደስ የመፍታት ልምዱን ተጠቅሞ፥ ከህዝቡ ጋር በመሆን እንፈታዋለንም ነው ያለው።