አዲሰ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በባህር ዳር ከተማ በርካታ ህገ ወጥ ጥይትና የጦር መሳሪያ መያዙን የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በዚህም በህገ ወጥ መልኩ የተያዙ 4 ሺህ 258 የክላሽ ጥይት እና 17 ስታርተር ቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
እንዲሁም ህገ ወጥ ጥይትና የጦር መሳሪያውን የያዙ ሁለት ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ከህብረተሰቡ ባገኘው መረጃ መያዝ መቻሉን ገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ ቤት ተከራይተው ሲኖሩ የቆዩ ሲሆን፥ አከራዮች የሚያከራዩለትን ግለሰብ በቂ መረጃ ካለመያዝ በመነጨ ድርጊቱ መፈፀሙን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በቀጣይም ሁሉም አከራይ የተከራዩን በቂ መረጃ በመያዝ እንዲህ አይነት ወንጀሎችን በመከላከል እና ከተጠያቂነት ራስን ነፃ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
እንደ አማራ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጻ፥ ህገ ወጥ መሳሪያዎቹም ሆነ ጥይቶቹ ሳይከፋፈሉ መያዛቸው የህብረተሰቡና የፖሊስ ሃይሉ ቅንጅት እየጠነከረ መምጣቱን ያሳያል፡፡
በቀጣይም ማንኛውንም የሚያጠራጥር ነገሮችን ህብረተሰቡ ሲመለከት በአማራ ፖሊስ ኮሚሽን የመረጃ ስልክ 0582201921 ለባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ 0582264666 በመደወል መረጃ መስጠት የሚቻል መሆኑን ገልጿል፡፡