Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለስምንት ሃገራት አዲስ አምባሳደሮችን ሾሙ


አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ አዲስ ለተሾሙ ስምንት አምባሳደሮች በተዘጋጀ የሽኝት ፕሮግራም ላይ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አምባሳደሮች በሚሄዱባቸው ሃገራት ቀድሞ የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ለሃገራቸው ጥቅምና ዕድገት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

አምባሳደሮቹ ከሃገራቱ ጋር ያለው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ፣ የዲፕሎማሲ፣ የመግባባትና የወዳጅነት ግንኙነት እንዲቀጥል ከማድረግ ባሻገር ግንኙነቱን በማሳደግም የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።

ከዚህ ባለፈም አዲስ የግንኙነትና የወዳጅነት ምዕራፍ እንዲኖራቸው ጠንክረው መስራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

ከተሿሚዎች መካከል አቶ ሬድዋን ሁሴን በአየርላንድ፣ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ በጣልያን፣ አቶ ቶሎሳ ሻጊ በኡጋንዳ፣ አቶ ፀጋዬ በርሄ በእስራኤል እና አቶ ረጋሳ ከፍአለ በጋና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ያገለግላሉ፡፡

በተጨማሪም አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በግብጽ፣ አቶ አብዱልአዚዝ አህመድ በኩዌት እንዲሁም አቶ ግርማ ተመስገን ደግሞ በኮትዲቯር የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ስራቸውን ያከናውናሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፥ “የሃገሪቱን የልማት ጉዞ የማስቀጠሉ ስራ በውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የውጭ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ያላቸው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም” ብለዋል፡፡

ስለሆነም ከውጭ የሚመጡ መልካም ዕድሎችን የመጠቀምና ተግዳሮቶችን በጥበብ የመሻገር ኃላፊነት በዋናነት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በስሩ በሚገኙ ኤምባሲዎች ትከሻ ላይ የወደቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ተሿሚ አምባሳደሮችም የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግስት አደራ በብቃት ለመወጣት ተጨማሪ አቅምና መነሳሳት የሚፈጥርላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።