አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የማልማትና የመጠቀም አቅም እየፈጠረች መምጣቷን ያረጋገጠ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የጋራ ምክር ቤቱ አራት የአባልነትና አንድ ወደ አባልነት የመመለስ ጥያቄዎች ከአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርበውለታል።
የጋራ ምክር ቤቱ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አባል ፓርቲዎች በህዳሴው ግድብ ያደረጉትን የመስክ ጉብኝት ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሯል።
ፓርቲዎቹ ባካሄዱት ጉብኝት የግድቡ ግንባታ በቀን ለ24 ሠዓታት ያለማቋረጥ እየተከናወነ መሆኑን በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸው በሪፖርት ቀርቧል።
የግድቡ ግንባታ በአገር ውስጥ አቅም በጥራትና በፍጥነት እየተከወነ መሆኑን መገንዘቡን የገለፀው ምክር ቤቱ ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም መጀመሯን ያሳያል ብሏል።
ይህም ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት የሚሆን ተግባር እንደሆነ ነው የገለጸው።
የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች በሰጧቸው አስተያየቶች የግድቡ ግንባታ ያለ ዕረፍት መካሄድ መቀጠሉ የኢትዮጵያውያን ድጋፍ በተግባር ታሪክ ለመስራት እየዋለ መሆኑን አስገንዝቦናል ብለዋል።
በግድቡ አካባቢ በቂ የሰራተኞች መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም የባንክ፣ የፖስታ፣ የሞባይልና የህክምና አገልግሎቶች መዘርጋታቸውን እንደተመለከቱም ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚካሄዱ የመንደር ማሰባሰብና የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የገለፁት ፓርቲዎቹ በተለይ የግብርና ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው ከአራት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀረበለት የአባልነት ጥያቄ ላይ መክሯል።
ጥያቄ ያቀረቡት ፓርቲዎች ሰነዶቻቸውን አሟልተው ሲቀርቡ እልባት ለመስጠትም ውሳኔ አሳልፏል።
ከምክር ቤቱ አባልነት ወጥቶ የነበረ አንድ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ላቀረበው የልመለስ ጥያቄም ፓርቲው በይፋ ይቅርታ ሲጠይቅ ጉዳዩ እንደሚታይ ከስምምነት ተደርሷል።
በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተፈጠረውን ድርቅ የምክር ቤቱ አባላት በአካል ተገኝተው መመልከት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በጋራ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ዕቅድ መሰረት በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመከራከር መድረኮች እንደሚዘጋጁ ተመልክቷል።
የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 9 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው።