አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሃማት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው ሙሳ ፋቂ መሃማት ህብረቱን ለቀጣይ አራት አመታት በሊቀመንበርነት ለመምራት የተመረጡት።
ጋናዊው ክዌሲ ቋርቴይ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
ምርጫው እስከ 7ኛ ዙር የተካሄደ ሲሆን በመጨረሻው ዙር ነው ቻዳዊው ሙሳ ፋቂ መሃማት ያሸነፉት።
የ56 አመቱ ሙሳ መሃማት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ማገልግል ችለዋል።
ፖለቲካኛው ሙሳ ከ2007 እስከ 2008 ባለው ጊዜም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል።
በዚያው ዓመት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ማገልገላቸው ግለ ታሪካቸው ያሳያል።
ሙሳ የአገሪቷን ሁለት ተቋማት በሚኒስትርነት የመሩና የቻድ የስኳር ኩባኒያንም በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸው ታውቋል።
የፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ካቢኔ ዳይሬክተርና የ2001 ምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሐመድ፣ ቦትስዋናዊቷ ፔሎኖሚ ቬንሰን-ሞታይ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አጋፒቶ ምባ ሞኩይ እና ሴኔጋላዊው ዶክተር አብዱላዪ ባዚልይ ከሙሳ ፋቂ መሃማት ጋር ህብረቱን በሊቀመንበርነት ለመምራት ተፎካክረዋል።
ዶክተር ኒኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን ላለፉት አራት አመታት በሊቀመንበርነት መምራታቸው ይታወቃል።
One Response to ሙሳ ፋቂ መሃማት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ