አዲስ አበባ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፁ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለግድቡ የምናደርገውን ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የገንዘብ ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ግድቡ የመላው ኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት መሆኑን የገለፁት ፓርቲዎቹ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ፓርቲዎቹ ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለተፋሰሱ አገራት ያለውን ፋይዳ ለማሳየት የምናደርገውን ዲፕሎማቲክ ጥረት እንገፋበታለን ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር /ኢፍዴኃግ/ ሊቀ-መንበር አቶ ገረሱ ገሳ እንደገለፁት ፓርቲያቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በአገሪቱ የሚካሄዱ የልማት ፕሮጀክቶችን ይደግፋል።
“ልማትን እየተቃወሙ የሚካሄድ ትግል የለም” ያሉት አቶ ገረሱ “ለህዳሴው ግድብ ያለን ድጋፍ እስከ ፍፃሜው የሚዘልቅ ነው” ብለዋል።
የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ ደግሞ “ግድቡ የአንድነት አካል በመሆኑ ድጋፍ ማድረግ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም” ብለዋል።
“ግድቡ የመንግስት ወይም የአንድ ፓርቲ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት ነው” ያሉት አቶ አየለ ድጋፋችን ዘላቂ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በግድቡ ላይ የተሳሳተ አመለካከት ያላቸውን አካላት ለማረም ሁሉም ዜጋ የአገሩ ዲፕሎማት ሆኖ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ /ኢዴአን/ ፕሬዝዳንት አቶ ጉዕሽ ገብረስላሴ በበኩላቸው ፓርቲያቸው የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ድጋፍ እያደረገ ነው።
“ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚፈልግ ካልሆነ በስተቀር በጋራ ተጠቃሚነት የሚያምን አገርም ሆነ ግለሰብ ግድቡን የሚቃወምበት ምክንያት የለም” ብለዋል።
“በአገራችን ማንም ጣልቃ ገብቶ እንዲፈተፍት አንፈቅድም” ያሉት አቶ ጉዕሽ የግድቡን ግንባታ የማይደግፉ አካላት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ፓርቲያቸው በንቃት እንደሚከታተል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው እንዳሉት “የግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ኢዴፓ ድጋፉን እየሰጠ ነው”።
ፓርቲው ለግድቡ ሲያደርጋቸው የቆዩ ዴፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
ፓርቲዎቹ ለግድቡ የሚያደርጉትን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከማጠናከር ባሻገር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚገፉበት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ58 በመቶ በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ።