አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 25 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከእስራኤል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥና ስልጠና ለማካሄድ ተባብራ መስራት እንደምትፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የእስራኤሉን የጋሊሊ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆሴፍ ሺቬልን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ በእስራኤል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በልምድ ልውውጥና ስልጠና መስክ ተባብራ የመስራት ፍላጎት አላት።
በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ170 በላይ ከሚሆኑ ሃገሮች ጋር በትብብር ከሚሰራው ከጋሊሊ ዓለም አቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር ለመስራት እንደምትፈልግ ነው የተጠቆመው።
ኢትዮጵያ በአቅም ግንባታ፣ በአመራር ክህሎት፣ በሥራ አመራር፣ በግብርናና በትራንስፖርት ዘርፎች ልምድ መቅሰም እንደምትሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ለዚህም መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጋሊሊ ዓለምአቀፍ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆሴፍ ሺቬልን በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው መስኮች ኢንስቲትዩቱ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በተለይ በግብርና እና በውሃ ቴክኖሎጂ፣ በወተትና በወተት ተዋጽኦ እንዲሁም በትራንስፖርት ዘርፍ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት ከመንግስት ጋር ተባብሮ ለመስራት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የእንስሳት ሃብት ዘርፍን እንደሚያጠቃልል ጠቅሰው፤ ይህም ከአጫጫር ሥልጠና እስከ ነፃ የትምህርት እድል እስከመስጠት የሚዘልቅ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
እስራኤል በንድፈ ሃሳብና ክህሎት ሥልጠና የተሽከርካሪ አደጋን 50 በመቶ መቀነስ መቻሏን ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህን ተሞክሮ በማካፈል በሃገሪቷ የሚደርሰውን ጉዳት በ20 በመቶ ለመቀነስ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።