አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ በምታደርገው ጥረት ኔዘርላንድስ ድጋፍ እንደምታደርግ የሀገሪቱ ፓርላማ አባላት ቡድን ገለጹ።
የኢትየጵያና የኔዘርላንድስ የፓርላማ አባላት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱም ድህነትና ሥራ አጥነት፤ የህገወጥ ስደትና የአሸባሪነት ተግባር ዋነኛ መንስኤዎች በመሆናቸው ችግሮቹን ለመፍታት ሁለቱም ሀገራት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ኢትዮጵያ ለወጣቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ፖሊሲ ቀርጻ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የህገ ወጥ ስደት መንስኤ ከምንጩ ለማድረቅ በቁርጠኝነት እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ከ800 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት አቶ ተስፋዬ፥ ስደተኞችን በማገዝ በኩል ከአውሮፓ ህብረት በተለይ ደግሞ ከኔዘርላንድስ ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያና አጋሮቿ አልሻባብን በማጥቃት ላይ ይገኛሉ ያሉት ሰብሳቢው፥ በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ለሠላም ጠንቅ ወደማይሆንበት ደረጃ መደረሱን አስረድተዋል።
አንዳንድ ጸረ ሠላም ኃይሎች በፈጠሩት ሁከት የኢትዮጵያ ሠላም ወደ መታወክ ደረጃ ደርሶ የነበረ ቢሆንም መንግስት ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሁሉም ነገር ወደ መረጋገት ደረጃ እንደተመለሰ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የኔዘርላንድስ የፓርላማ አባላት ቡድን መሪ ሎስ ይፕማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ በምታደርገው ጥረት የኔዘርላንድስ ድጋፍ እንደማይለያት አረጋግጠዋል፡፡
ኔዘርላንድስ ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን ያነሱት ሎስ ይፕማ፥ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቅ ደረጃ ለማሸጋገር ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።
የኔዘርላንድስ ፓርላማ ልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ ቆይታቸው የተለያዩ የስደተኛ ካምፖችን ይጎበኛሉ።
መረጃውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ያደረሰን።