Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማምረቻ ዘርፉ እንዲሰማሩ ለማገዝ የ7 ቢሊየን ብር ብድር መዘጋጀቱ ተገለፀ

local-investors
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማምረቻ ዘርፉ እንዲሰማሩ ለማገዝ የሚያስችል የ7 ቢሊየን ብር ብድር መዘጋጀቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴርሩ እንደገለጸው፥ ብድሩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል ለማምረቻ መሳሪያዎች መግዢያ የሚያገለግል ነው።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው፥ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በማምረቻ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚከናወኑ ስራዎች ባለሃብቱን የሚያነቃቁ መሆናቸውን ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይደመጣሉ።
ባለሀብቶች ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን የመሬት አቅርቦት፣ ገንዘብና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማቅረብ የሚሰሩ ስራዎች ደጋፊ ቢሆኑም ጥቃቅን የሆኑ ችግሮች ግን ለዘርፉ ማነቆ ሲሆኑ እንደሚታዩ ይናገራሉ።
በጉምሩክ አካባቢ ያሉ የተንዛዙ አሰራሮችና የሃይል አቅርቦት እጥረትን በማሳያነት ይጠቅሳሉ።
የፓን አፍሪካ ንግድና ኢንደስትሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና፥ መንግስት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶችን ወደ ዘርፉ ለማሰማራት ሲያስብ ከሌሎች መሰል ሀገራት በተሻላ ሀገሪቱን እንዲመርጡ የሚያስችል ድጋፍ ማቅረብና ከገቡም በኋላ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት ይጠቁማሉ።
ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ይናገራል። የቦሌ ለሚ እና የሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታንም ማሳያዎች ናቸው ይላል።
በኢንደስትሪ ፓርኮቹ አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች የተሟላላቸው በመሆኑ በፓርኮቹ የተዘጋጁት 37 ሼዶች እንዲሁም በማስፋፊያ የተያዙት 15 ሼዶች ሙሉ በሙሉ በአለም አቀፍና ታዋቂ አምራቾች ሊያዙ መቻላቸውን በኮርፖሬሽኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ገመቹ ይገልጻሉ።
በፓርኮቹ የሀገር ውስጥ የማምረቻ ተቋማት መግባት መቻላቸውም አለማቀፍ ልምድንና ተሞክሮን ለመቅሰም አስችሏቸዋል ነው የሚሉት።
በቀጣይም በባህር ዳር፣ ጅማ፣ አዳማ፣ መቀሌና ደብረ ብርሃንን ጨምሮ በ10 ከተሞች የሚገነቡት የኢንደስትሪ ፓርኮች ግንባታቸውን ከማፋጠን ጎን ለጎን ወደ ፓርኩ የሚገቡ ባለሃብቶችን የማፈላለጉ ስራም ጎን ለጎን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፓርኮቹ ግንባታም ከ6 እስከ 9 ወራት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችና አቅርቦቶችም ጎን ለጎን የሚከናወኑ ነው የሚሆነው ይላሉ አቶ ጥላሁን ።
ለማምረቻ ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታን ከሚፈጥሩ ነገሮች አንዱ ዝግጁ የሆነ የማምረቻ ቦታ ቢሆንም ዘርፉ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚፈልግ እንደሆነ ባለሀብቶች ይናገራሉ።
በኢንደስትሪ ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አበባው፥ ከዚህ አንጻር ይህንን ችግር በመቅረፍ ባለሀብቶችን ሊደግፍ የሚችል እቅድ እንደተዘጋጀ ይናገራሉ።
ባለሃብቱ የሚያስፈልገውን መሳሪያ በሊዝ እንዲያገኝ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል 7 ቢሊየን ብር ብድር ለዚህ ዓመት መያዙን ይገልጻሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን በስፋት ወደ ማምረቻው ዘርፍ ለማስገባት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወደ ማምረቻው ዘርፍ የገቡትንም በሙሉ አቅማቸው እንዲጠቀሙና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለመደገፍ የተያዘውን አቅድ ለማሳካት የሚያስችል ስራ እያከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ ያነሳሉ።
የአቅም ግንባታን ማከናወን አንዱ ሲሆን፥ የኢንደስትሪ ልማት ግብዓት ድርጅት አቅምን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል እቅድም ተይዟል።
በተለይ ደግሞ አነስተኛና መካከለኛ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ስራም እየተሰራ ነው ብለዋል።