Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የህዳሴ ግድብ በተቀመጠለት ዲዛይንና የጊዜ ሰሌዳ ግንባታው ቀጥሏል

grd
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሰራተኞች ላባቸው እየተንጠባጠበ የዕለት ስራቸውን ያከናውናሉ።
ትልልቅ ተሽከርካሪዎች ኮንከሪት፣ ብረታ ብረትና አሸዋ ጭነው ያለ ዕረፍት ይመላለሳሉ።
ግንባታው በሚካሄድበት ጉባ አካባቢ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣው፣ የብረታ ብረት ስራው ሲካሄድ የሚሰማው ድምጽ አካባቢው በስራ ላይ ስለመሆኑ ያረጋግጣል።

ተሽከርካሪዎች በፍጥነት በየቦታው ደርሰው ወደ ምሳ፣ እራትና ዕረፍት ቦታዎች በትጋት የሚሰሩትን ሰራተኞች ያመላልሳሉ።
ከዕረፍት ወደ ስራ የሚገቡትን ሙያተኞች ወደ የምድብ ቦታዎች ያደርሳሉ። ስራው ሌትም ሆነ ቀን ያለማቋረጥ ይከናወናል።
“ግንባታው ለሰከንድም ሳይቋረጥ በከፍተኛ ጥንቃቄና ኃላፊነት በመካሄድ ላይ ነው” በማለት ነው የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የገለጹት።

ሚኒስትሩ በጉባ ምልከታ ሲያደርጉ ላነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ስራ 54 በመቶ ተጠናቋል።
“በህዝብና በመንግስት ድጋፍ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ ለአገሪቱ የኢንዱስትሪ ሽግግር ዋነኛ አቅም ይሆናል” ያሉት ሚኒስትሩ መንግስት ለዚህ ፕሮጀክት ከየትኛውም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ መስጠቱን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በበኩላቸው የዋናው ግድብ አጠቃላይ ስራ፣ የኤሌክትሪክና የኃይድሮሊክ ስራዎች፣ የውሃ ማስተንፈሻና ሌሎችም መሰረታዊ ግንባታዎች በተቀመጠላቸው ዲዛይን መሰረት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ የግድቡ ግንባታ ሂደት ዋናው ግድብ ከሚያርፍበት ቦታ ላይ መገንባት ካለበት 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአርማታ ሙሌት ውስጥ 7 ሚሊዮን ያህሉ ተከናውኗል።
የውሃ ፍሰቱን ወደ ዋናው ግድብ አቅጣጫ የሚያመጣውና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የሳድል ዳም ስራ መሰራት ካለበት 15 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአለት ሙሌት ውስጥ ስምንት ሚሊዮን ያህሉ ተከናውኗል።
ኢንጂነሩ እንዳሉት “የግድቡ ግንባታ በወቅቶች መፈራረቅ ሳይበገር 11 ሺህ ሰራተኞች በሶስት ፈረቃ ክረምት ከበጋ ሌሊትና ቀን ሳይሉ እየሰሩ ይገኛሉ”።
የግድቡ የሲቪል ስራ በጣልያኑ ሳሊኒ ኩባንያ እና በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችለውን ግድብ ለመገንባት የኢትዮጵያዊያን ሙያተኞች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መጋቢት 2004 ዓም ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአገሪቱን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር የአባይ የታችኛው ተፋሰስ አገራትንና ጎረቤት አገራትንም ያግዛል።