Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ከኦነግ አመራሮች ገንዘብ በመቀበል አባላትን ለመመልመልና ስልጠና ለመስጠት ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ 17 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

charge
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ በሽብርተኛ ድርጅትነት ከተፈረጀው እና አሜሪካ ከሚገኘው የኦነግ የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ በአዲስ አበባና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ አባላትን በመመልመልና ስልጠና ለመስጠት ከቡድኑ አመራር ገንዘብ በመቀበል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛው የሽብር ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሳቸው መነበብ ጀምሯል።

1ኛ ተከሳሽ ድሪብሳ ዳምጤ፣ 2ኛ ሰኚ ዱጋሳን ጨምሮ 17 ግለሰቦች ናቸው ክሱ የተመሰረተባቸው።

ነዋሪነታቸውንም አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሰበታ፣ ጅግጅጋ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ያደረጉ ናቸው።

ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ በሚጠራውና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው አሸባሪ ቡድን አባል በመሆን ተንቀሳቅሰዋል ይላል ክሱ።

ከሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል የሚለውም በክሱ ተጠቅሷል።

በሀገር ውስጥ አባላትን በመመልመልና በማደራጀት የኢትዮጵያን መንግስት በትጥቅ ትግል በሀይል የመለወጥ የፖለቲካ አላማ በመያዝ የሀገሪቱን ህገ መንግስታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማትን ለመናድ እና ለማፈራረስ ሲሰሩ እንደነበርም ክሱ ያስረዳል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ጫካዎችን በማጥናት፣ ወታደራዊ ካምፕ በመመስረት እና አባላትን በህዋስ በማደራጀት ወታደራዊ ስልጠና ሰጥተዋል ነው ያለው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በክሱ።

ይህን አላማቸውን ለማሳካትም አሜሪካ ከሚገኙ የኦነግ የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራሮችና ከጀዋር መሀመድ ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ ለስልጠና እና ለሽብር ተግባራቸው መፈፀሚያ በተለያዩ ጊዜያት 157 ሺህ ብር መቀበላቸው ተጠቁሟል።

በተቀበሉት ገንዘብም አዲስ አበባ ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ በመሄድ ለጊዜው ማንነቱ ካልታወቀ ግለሰብ ሶስት ክላሽ የጦር መሳሪያ ከ95 ጥይት ጋር በመግዛት በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኝ አፋ ጫካ በመግባት ወታደራዊ የአካል ብቃት ስልጠናን ጨምሮ የመሳሪያ መፈታታት እና መገጣጠም እንዲሁም የተኩስ ኢላማ ስልጠና መስጠታቸው ነው በክሱ የተጠቀሰው።

ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ላይ ተቃውሟቸውን ለማድመጥ ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

.