Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በኢሬቻ በዓል ላይ በተነሳው ሁከትና ግርግር በጠፋው የሰው ህይወት ማዘናቸውን ገለጹ

hd-on-erecha
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በኢሬቻ በዓል ላይ በተነሳው ሁከትና ግርግር በጠፋው የሰው ህይወት ማዘናቸውን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው እና ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት በዓል መሆኑን አንስተዋል።
ይህንን በዓልንም ዘንድሮ በድምቀት ለማክበር የኦሮሞ አባገዳዎች ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በዓሉን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም እንዲሆን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ሲሰራ ቆይቷል ነው ያሉት ።
በዚህም መሰረት ዛሬ ህዝቡ በዓሉ የሰላም እና የመቻቻል እንዲሁም ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት መሆኑን ለማስመስከር በዓሉ ወደ ሚከበርበት ቢሾፍቱ ሆራ ሀይቅ መትመሙንም ገልፀዋል።
ክብረ በዓሉን አባገዳዎች ለማስጀመር ሂደቱን ለመምራት በሚዘጋጁበት ወቅት ነውጠኛ ሀይሎች ቀደም ብለው በተዘጋጁት መሰረት በዓሉን የነውጥ እና የብጥብጥ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም የገለፁት።
በዚህ ሂደት ውስጥ በተቀሰቀሰ ግርግር በበዓሉ ላይ የነበሩ እርስ በርስ በመረጋገጥ እና አከባቢው ገደላማ በመሆኑ ገደል ውስጥ በመግባታቸው 52 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን፤ ቁጥራቸው ተቀራራቢ የሆኑ ሰዎችም መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
ሁኔታው አሳዛኝ እና አስከፊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጠፋው የሰው ህይወት በኢፌዴሪ መንግስት እና በራሳቸው ስም የተሰማቸውን ሀዘን ገልፃዋል።
ለሟች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች እና ለመላው ኢትዮጵያውያን ም መፅናናትን ተመኝተዋል።
ሁኔታው ሊፈጠር የማይገባ ነበር ያሉት አቶ ሀይለማርያም፥ በዓሉ የፍቅር፣ የመቻቻል እና ፈጣሪን የማመስገኛ እንደመሆኑ ከኦሮሞ ህዝብ ባህል ባፈነገጠ መልኩ የነውጥ ሀይሎች የፈፀሙት ድርጊት እጅግ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
መላው የኦሮሞ ህዝብም ሆነ መላው ኢትዮጵያዊ ይህን እኩይ ተግባር ከመንግስት ጎን ቆመው እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።
የዜጎች ህይወት እንዲያልፍ ምክንያት የሆኑትን ወገኖች መንግስት በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ በመጠቆም ህዝቡ ይህን እንዲያግዝ ነው ያሳሰቡት።
መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን፤ በሁከቱ ወቅትም ምንም የጥይት ድምፅ አለመነሳቱን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፀጥታ ሀይሎች ሰላምን ለማስከበር ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ህዝቡ መንግስት የጀመረውን የሰላምና የለውጥ እንቅስቃሴን እንዲደግፍም አያይዘው ጠይቀዋል።