አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 26፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የበደሌ ከተማ እና አካባቢዋ ያሉ ወረዳዎች ዞን ለመሆን ላቀረቡት ጥያቄ የኦሮሚያ ክልል መንስት ምላሽ ሰጠ።
በዚህም ህብረተሰቡ በቀረበው ጥያቄ መሰረት አካባቢው የቡኖ በደሌ ዞን ተብሎ እንዲጠራ መወሰኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
ይህንን በማስመልከት በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙክታር ከድር፥ መንግስት ከህዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡ እያነሳ ከነበረው ጥያቄ ውስጥ አንዱ የሆነው የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳደሮችን በቅርበት ማግኘት እንፈልጋለን የሚለው አንዱ ነው ያሉት ርእሰ መተዳደሩ፥ ለዚህም ምላሽ መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት ወደ ፊትም ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የመልካም አስተዳዳር እና ሌሎች ጥያቄዎች ትኩረት በመስጠት ደረጃ በደረጃ እየፈታ ይሄዳል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሙክታር አያይዘውም የዞኑ ነዋሪዎች የሰላም አምባሳደሮች ናቸው ያሉ ሲሆን፥ አሁንም የአካባቢያቸውን ሰላም የማስጠበቁን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ዞን የመሆን ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ደስታቸውን ከሚኖሩበት አካባቢ እስከ በደሌ ከተማ ሰልፍ በመውጣት መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የበደሌ ከተማ እና በአካባቢዋ የሚገኙ ወረዳዎች ከዚህ ቀደም በኢሉ አባቦራ ዞን ስር ይተዳደሩ እንደነበር ይታወቃል።