ኢትዮጵያ በዚህ ኦሎምፒክ ከቀደምቶቹ 6 ኦሎምፒኮች ያነሰ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በሲድኒው እና በቤጅንግ ኦሎምፒክ አራት፣ አራት ወርቅ በማምጣት ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሜዳሊያ ያመጣችበት ወቅት ነው፡፡
በሲድኒው ኦሎምፒክ ሀይሌ ገብረ ስላሴ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ገዛኸኝ አበራ እና ደራርቱ ቱሉ ወርቅ ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
ቀጥሎ በተካሄደው በቤጂንግ ኦሎምፒክ ደግሞ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ ሁለት፣ ሁለት ወርቅ በማምጣት ሀገራቸውን በደረጃዋ ክፍ እንድትል አስችለዋል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት በተደረገው የለንደን ኦሎምፒክም ኢትዮጵያ ሶስት ወርቆችን በጥሩነሽ፣ መሰረት እና ቲኪ ገላና ማግኘት ችላለች፡፡ በቀሪዎቹ ውድድሮች ሁለት፣ ሁለት ወርቆችን ማግኘትም አልተሳናትም፡፡
በብራዚሏ ሪዮ ዲጄኔሮ የተዘጋጀው ኦሎምፒክ ግን ለኢትዮጵያ ፊቱን ያዞረ ውድድር ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በአልማዝ አያና ብቸኛ ወርቅ ብቻ ተመላሽ ሆናለች፡፡ ሁለት ብር እና 5 ነሐስም አግኝታለች፡፡
ጎረቤታች ኬንያ በአንጻሩ በታሪኳ የመጀመሪያውን ከፍተኛ ሜዳሊያ ሰብስባለች፡፡ በቤጂንግ ኦሎምፒክ 6 ወርቅ ማግኘቷ የሚታወስ ቢሆንም በሪዮ ኦሎምፒክ ተመሳሳይ ወርቅ እና የተሻለ የብር ሜዳሊያ ይዛለች፡፡
ኬንያ ከባለፉት 6 የኦሎምፒክ ዉድድሮች በሁለት ኦሎምፒኮች ብቻ ኢትዮጵያን በልጣለች፡፡ ይህም በቤጅንግ እና በሪዮ ኦሎምፒክ ነው፡፡ በቀሪዎቹ አራት ውድድሮች ኢትዮጵያ ከኬንያ ብልጫ የወሰደች መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ልዩነቱ ግን ሰፊ አልነበረም፡፡
ኢትዮጵያ በለንደን እና ሪዮ ኦሎምፒክ በወከለቻቸው ወንድ አትሌቶች ወርቅ ማምጣት አልቻለችም፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ በወንዶች ወርቅ ማግኘት ያቆመችው በቤጂንጉ ኦሎምፒክ በቀነኒሳ ዘመን ከነገሰች በኋላ ነው፡፡ በዘንድሮው ውድድር የሴቶች ሚናም ቀንሶ ታይቷል፡፡
በአትሌቲክሱ ወርቅ የለመደውን ህዝብ እንደለመደው ወርቅ ለመስጠት ፌደሬሽኑ ከጎረቤቱ ኬንያ ተሞክሮ ሊወስድ ይገባል፡፡
source: EBC