አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የተቀመጠው ብሄራዊ አርማ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች ህዝቦችና ሃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነታቸውን ያንጸባርቃል።
ይህንን በሚጻረር መልኩ ብሄራዊ አርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ የብሄረሰቦችን እና የሃይማኖትን እኩልነት ብሎም በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተውን አንድነት አለመቀበል መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሪፐብሊኩን ሉዓላዊነትና እና የህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት መገለጫ ሲሆን፥ ይህም የሰንደቅ ዓላማው ምንነት ማሳያ ነው።
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊነታቸው እና ፈቅደው የመሰረቱት አንድነትም በሰንደቅ ዓላማው ተገልጿል።
በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚገኘው ብሄራዊ አርማ መለያም፤ ሰማያዊው መደብ ሰላምን፣ ቀጥታ ያሉት መስመሮች ደግሞ የብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦችንና የሃይማኖት እኩልነትን፣ ከመስመሮቹ የተዋቀረው ኮኮብ የሃገሪቱ ህዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የመሰረቱትን አንድነት እና ቢጫው ደግሞ ለህዝቦች የተፈነጠቀውን ተስፋ ያሳያል ነው ያሉት፥ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ በሪሁ ተወልደብርሃን።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛው አቶ ጳውሎስ ኦርሺሶ በበኩላቸው፥ የሀገሪቱ ሉዓላዊነት እና በመፈቃቀድ ላይ ለተመሰረተው አንድነት መገለጫ ለሆነው ሰንደቅ አላማ ዜጎች ተገቢውን ክብር መስጠት እንዳለባቸው ህግ ያስገድዳል ይላሉ።
ይሁንና ህጉ ለሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ከፍተኛ ጥበቃ ቢያደርግም የፌደራሉን መንግስት የማይወክሉ ሰንደቅ ዓላማዎች በማህበራዊ ሚዲያ በተጠሩ ህገወጥ ሰልፎች አማካኝነት አደባባይ ላይ ውለዋል።
በአንዳንድ ስፍራዎች ደግሞ የሪፐብሊኩን ሰንደቅ ዓላማ ህጋዊ እውቅና በሌለው ሰንደቅ ዓላማ ለመተካት ሙከራ ተደርጓል።
አቶ በሪሁ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ በሌላ ተተክቷል ማለት፤ የሀገሪቷ ሉዓላዊነት ተደፍሯል የሚል የህግ ትርጓሜን ይሰጣል ባይ ናቸው።
በህግ የተደነገገው የፌደራል መንግስት ሰንደቅ ዓላማ ወርዶ ሌላ ሰንደቅ ዓላማ ተሰቅሏል ማለት የሃገሪቱ ምልክት ተደፍሯል ማለት መሆኑንም አስረድተዋል።
ህገ መንግስቱ፣ ሰንደቅ ዓላማ እና ሃገሪቱ የምትወከልባቸው ሌሎች ልዩ ምልክቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሀገር ሉዓላዊነት መደፈሩን ማሳያዎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ አንቀጽ 23 መሰረት ላይ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ቃላቶችን መጻፍ፣ ሌሎች ምልክቶችን ወይም አርማዎችን አልያም ስዕሎችን ለጥፎ ከመገልገል አንስቶ፥ ሰንደቅ ዓላማው በሚሰቀልበት እና በሚወርድበት ጊዜ ተገቢውን ክብር አለመስጠት የተከለከሉ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
አቶ በሪሁ እንደሚሉት፥ ብሄራዊ አርማ የሌለውን ሰንደቅ ዓላማ መያዝም አንድ የሪፐብሊኩን ሉዓላዊነት እና የህዝቦችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት መናድ ነው።
ጨለምተኝነት፣ ጸረ ሰላም እና ሰንደቅ ዓላማውንና የሚወክለውን ህዝብ አለመቀበል መሆኑንም ይገልጻሉ አቶ በሪሁ።
ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ህገወጥ ሰልፎች ላይም፥ በህገ መንግስቱ እውቅና ያለውን የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በሌላ የመተካት ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
ይህን እና መሰል ወንጀሎች ሲፈጸሙ ጣራው እስከ ሶስት አመት ሆኖ ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል የእስር ቅጣት እንደሚያስከትል የተናገሩት ደግሞ አቶ ጳውሎስ ናቸው።
የወንጀል ድርጊቱ ፈጻሚ ድርጅት ከሆነ ደግሞ፥ የህግ ተጠያቂነት ወሰኑ ከአንድ መቶ እስከ 500 ሺህ ብር እንደሚደርስም ያስረዳሉ።
ከዚህ ባለፈ ግን ተያያዥ እና ተደራራቢ ወንጀሎች ተፈጽመው እንደሆነ በራሳቸው የወንጀል ድርጊትን በማቋቋም ተጠያቂነትን ያስከትላሉም ብለዋል።