Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት በህግ ቢታገድም በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ዱባይ ይገባሉ

h

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪትን በህግ ቢያግድም በጉብኝት፣ በንግድ ቪዛ እና በቤት ሰራተኝነት ስም በሚላኩ ቪዛዎች በተለያዩ አየር መንገዶች አማካኝነት በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ዱባይ በማምራት ላይ መሆናቸው ተነግሯል።

በዚህ መልኩ ወደ ዱባይ በማምራት ተቀባይ በማጣታቸውና የተሟላ ሰነድ አልያዛችሁም ተብለው ከዱባይ ባለፉት ቀናት ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ወጣቶች በደላሎች አማካኝነት ለዚህ ችግር መዳረጋቸውን እየተናገሩ ነው።

በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ስራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ተስፋው፥ የጉብኝትና ንግድ ቪዛውን ለሽፋን ተጠቅመው ዱባይ በህገወጥ መንገድ በቤት ሰራተኝነት የሚቀጠሩ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ችግር እንደሚዳረጉ ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከጉብኝትና ንግድ ቪዛ ባሻገር በቀጥታ ለቤት ሰራተኝነት በሚል ቪዛ አማካኝነት ወደ ዱባይ በብዛት የሚገቡ ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል።

በዚህ መልኩ ወደ ዱባይ ባለፈው አንድ አመት የገቡና ለችግር የተዳረጉ 5 ሺህ ኢትዮጵያውያንን በሀገሪቱ ካለው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጋር በመተባበር ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ነው ስራ አስኪያጁ የገለፁት።

ይህ ደግሞ የሰራተኝነት ውል ሳይገባ የሚደረግ የስራ ስምሪት በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑን ለከፋ ችግር ይዳርጋል ብለዋል።

በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንፅላ ጄኔራል ይበልጣል አዕምሮም፥ በአሁኑ ወቅት ዱባይ ከፍተኛ የቤት ሰራተኛ ስለምትፈለግ በቤት ሰራተኝነት መሰማራት በሚያስችል ቪዛ ሰም ጭምር ነው ኢትዮጵያውኑ ወደ ዱባይ የሚያመሩት ብለዋል።

በእርግጥ ቪዛው ህጋዊ ነው የሚሉት ቆንጽላ ጄኔራሉ፥ ችግሩ መንግስት ህጋዊውን ጉዞ ሳይጀምር እና ከሀገራቱ ጋር የስራ ሰምምነት ላይ ሳይደረስ ሰራተኛ ሆኖ ወደ ዱባይ የሚያመራው ዜጋ ሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ገብቶ ሳይፈራረም የሚሄድ በመሆኑ የሚፈጠር ነው ባይ ናቸው።

ይህ ደግሞ አካሄዱ እንጂ ኢትዮጵያውያኑ ዱባይ ከገቡ በኋላ ወደስራ የሚሰማሩበት መንገድ ህጋዊ ባለመሆኑ ዋስትናን ለሰራተኛው ያሳጣል ብለዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ በተለያዩ አየር መንገዶች አማካኝነት በገፍ ወደ ዱባይ እየገቡ ያሉ ዜጎች ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ የዱባይ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሰራተኛ የስራ ስምምት ሳይፈረም፤ በተለያዩ መንገዶች ከዱባይ በሚመጡ ቪዛዎች አማካኝነት ወደ ዱባይ ለሚያመሩ ዜጎች ዱባይ የስራ ፈቃድ እየሰጠች በማሰማራት ላይ መሆኗ ለህገወጥ ደላሎች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም አብራርተዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ በበኩላቸው፥ በጉብኝትም ይሁን በቤት ሰራተኝነት ቪዛ ስም ወደ ዱባይ የሚደረገውን ጉዞ ማስቀረት አይቻልም ብለዋል።

በአዲሱ የውጭ ሀገራት ስምሪት ህግ መሰረት ጉዞው ሲፈቀድ ዜጎች ህጋዊ የስራ ወል ፈርመው እንዲሄዱ ማድረግ ብቻ ነው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስልጣን ብለዋል አቶ ግርማ።

በመሆኑም ወደ ዱባይ በደላሎች አማካኝነት በጉብኝትና በቤት ሰራተኝነት ስም የሚደረግ ጉዞ ህገወጥ በመሆኑ ዜጎች ከዚህ ድርጊት እንዲቀጡ ነው የጠየቁት።

አዲሱ የውጭ ሀገራት ስምሪት ህግን ማስፈጸም የሚያስችሉት መመሪያና ደንብ እየተጠናቀቁ ነው ያሉት አቶ ግርማ፥ ደንቡን ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላክና መመሪያውን ደግሞ ወደ ሚኒስቴሩ በማቅረብ ከጸደቀ በኋላ ወደ ስራው ይገባል ብለዋል።

ደንብ እና መመሪያው እስኪጠናቀቅ ድረስ ግን እየተከሰተ ያለውን ችግር ህገወጥ ነው ከማለት ባለፈ በየቀኑ በእንዲህ መልኩ ራሳቸውን ለችግር እያጋለጡ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለመታደግ አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልጋል።

በብርሃኑ ወልደሰማያት