Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸው ታወቀ


የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከአባልነታቸው መነሳታቸው ተጠቆመ። ሰሞኑን ደግሞ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸው ተሰምቷል።

ከአቶ ለማ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት አመራሮችም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመልክቷል።

ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ እና ሌሎቹ ሁለት አባላት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነት እንዲነሱ የተወሰነው ጨፌ ኦሮሚያ ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ላይ እንደሆነም የሪፖርተር መረጃ ያመለክታል።

አቶ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለዋል በሚል ምክንያት ጨፌው ሌሎች አባላትን በመምረጥ እንዲተኩ ማደረጉን መረጃዎቹ አመልክተዋል።

ጨፌው በአቶ ለማ እና በሌሎቹ ሁለት አባላት ምትክ አዲስ አባላትን መርጦ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስታወቀ ሲሆን፣ አቶ ለማን ተክተው የተመረጡትም በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ኃላፊ እና በጨፌ ኦሮሚያ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።

በሌሎቹ ሁለት አባላት ምትክ ደግሞ የክልሉ ፓርቲ አደረጃጀት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻና አቶ አብዱል ሐኪም መመረጣቸው ታውቋል። የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ለማ ሰሞኑን በተካሄደ የፓርቲ ስብሰባ ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸውም ይፋ ሆኗል።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብስባ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ አቶ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸውን አስታውቋል።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ስብሰባና ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ስብሰባው በፓርቲው ክልላዊ መዋቅር ላይ የተስተዋሉ ድክመቶች ላይ በስፋት ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የተመለከቱ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ገልጸዋል።
በፓርቲው የክልል መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች ላይ ባደረገው ግምገማም በማዕከላዊ አባልነት ሲያገለግሉ የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ፣ ወ/ሮ ጠይባና ሚልኬሳ (ዶ/ር) ላልተወሰነ ጊዜ ከማዕከላዊ አባልነታቸው እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቀዋል።

አቶ ለማ መገርሳ ከማዕከላዊ አባልነታቸው እንዲታገዱ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ አለመገኘታቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የመከላከያ ሚኒስትር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተጣሉባቸው መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይም በተደጋጋሚ አለመገኘታቸውን አቶ ፍቃዱ በምክንያትነት አንስተዋል።

አቶ ለማ የአገር መከላከያ ሚኒስትርን በመወከል የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ሲሳተፉ አይስተዋሉም። አቶ ለማ ላይ ሌላው የቀረበው የዲሲፕሊን ጥሰት አባል በሆኑበት የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ስብሰባ ላይም በተደጋጋሚ አለመሳተፋቸውና ለሁለት ቀናት በተካሄደው የፓርቲው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጎላቸው አለመገኘታቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም አቶ ለማ ከማዕከላዊ አባልነታቸው ታግደው እንዲቆዩ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ስብሰባ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አስረድተዋል።

ወ/ሮ ጠይባም ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ ግጭቶች ጋር በተገናኘ ስማቸው ሲነሳ መቆየቱ ጠቁመው፣ ከፍተኛ አመራሩና አባሉም አመኔታ በማጣቱ ጥያቄ ያነሳ ስለነበር ጉዳያቸው እስከሚጣራ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲታገዱ መደረጉን ገልጸዋል።

ሚልኬሳ (ዶ/ር) ከፓርቲው ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ በውስጥ ማድረግ የሚገባን ትግል ወደ ውጭ በማውጣትና መገኘት በሚገባቸው ስብሰባዎች ላይ ሊገኙ ባለመቻላቸው እንዲሁም የፓርቲውን ሚስጥር በተለያዩ መድረኮች በማውጣታቸው ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን ገልጸዋል።

Source : Reporter