ረቡዕ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. 45ኛ የምሥረታ በዓሉን ያከበረው ሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ሰሞኑን ለበዓሉ አከባበር በመቀሌ ለተገኙ ጋዜጠኞች ከአራት ሰዓት ተኩል በላይ የፈጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ችግር እንዳለበት፣ ሜቴክ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ያላግባብ ስለመውጣቱ፣ በትግራይ ክልልና በክልሉ ተወላጆች ላይ የፖለቲካ ሴራ ስለመፈጸሙ፣ የፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሉ ተዋጊ ኃይል ስለመላኩ፣ ለውጡ ከተደረሰበት ስምምነት በተቃራኒ ስለመጓዙ፣ የሕወሓትና የብልፅግና ፓርቲ ጉዳይን በተመለከተ፣ እንዲሁም መጪውን ምርጫ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ላይ ከፖለቲካ ሴራ እስከ ተዋጊ ጦር በመላክ ወደ ውጊያ እንድንገባ እየተፈታተነን ነው፤›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ካልኖረ ግን፣ የትግራይ ሕዝብ ታግሎ ያረጋገጠው መብቱ እጁ ላይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
የ45ኛ የምሥረታ በዓሉን ረቡዕ የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ያከበረው ሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ላይ ከፖለቲካ ሴራ እስከ ተዋጊ ጦር በመላክ ወደ ውጊያ እንዲገቡ እየተፈታተናቸው መሆኑን አስታወቁ፡፡ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በርካታ ጉዳዮችንም አንስተዋል፡፡
ሊቀመንበሩ የድርጅታቸውን የምሥረታ በዓል በተከበረበት ዕለት በተለይም በትግራይ መንግሥትና በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ነው ባሉት ጥቃት፣ ስም ማጥፋት፣ እንዲሁም በአገሪቱ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ መንግሥትም ሆነ የተወካዮች ምክር ቤት እንዲያወግዙ በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት ጨምሮ፣ በአገራዊ ሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ሐሙስ የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ሰፊ ገለጻ ሰጥተው ነበር፡፡
ከአራት ሰዓት ተኩል በላይ በቆየው ገለጻቸው ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ድርድር ሒደት፣ በክልሉና በትግራይ ተወላጆች ላይ የፖለቲካ ሴራና ወደ ጦርነት የሚገፋፉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ስለመደረጋቸው፣ ባለፈው ዓመት የፌደራል መንግሥት በሕገወጥ መንገድ ተቋማዊ አሠራር ሳይጠብቅ የፖሊስ ኃይል ልኮ ኤርፖርት መማረካቸውን በተመለከተ፣ የለውጥ ሒደቱ የያኔዎቹ ድርጅቶች ከተስማሙበት የግምገማ ሒደት በተቃራኒው መሄዱን የሚመለከቱ፣ ከድኅረ ኢሕአዴግ ዘመን በኋላ ሕወሓት ከብልፅግና ጋር ስለሚኖረው አዲስ ውይይት፣ እንዲሁም ከመጪው ምርጫ ጋር ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እንዴት ክልሉን ስለማስተዳደርና ከፌደራል መንግሥት ጋር በልዩነት ስለሚያከናውኗቸው ጉዳዮች የተመለከቱ ይገኙበታል፡፡
የግድቡ ጉዳይ ትናንትና ዛሬ
ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በግል የሚሰማቸውን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡ ግድቡ ከጅማሬው አንስቶ በ2010 ዓ.ም. ወደ ክልሉ በአመራርነት እስከሄዱበት ድረስ ያለውን በማውሳት፣ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም እንዳሳዘናቸው ጠቁመዋል፡፡
‹‹በግሌ እጅግ አዝኛለሁ፤›› ያሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ መንግሥት አሁን እያደረገ ባለው ነገር የግድቡን ሥራ ወደ ኋላ ጎትቶታል ይላሉ፡፡ ግድቡን በራስ አቅም በመገንባት የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት እግረ መንገዱን የኃይል ምህንድስና ኢንዱስትሪዎች ለማቋቋም ይረዳ ነበር ብለው፣ ይህ ዕቅድ በአመራር ስህተት ተጨናግፏል ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹በተለይ ሜቴክ የአስተዳደር ጉድለቶች እንደነበሩበት በግል የማምን ቢሆንም፣ ችግሩን አስተካክሎ መሄድ ሲቻል ሙሉ በሙሉ ከሥራው ውጪ እንዲሆን መደረጉ ትክክል አልነበረም፡፡ ግድቡን በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቀን የመጀመርያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት ይጀምር ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ከምንም በላይ የሚያሳዝነው ከአምስት ዓመት በላይ በዚያ በረሃ የነበሩ ወጣት ልጆች እንዲበተኑ መደረጉ እንደ አገር ትልቅ ኪሳራ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹በግድቡ ግንባታ ሜቴክ በነበረው ድርሻ ሙሉ ለሙሉ ጥሩ መሐንዲሶች ማፍራት ችለን ነበር፡፡ ለወደፊትም በራሳችን አቅም ለመገንባት የሚችሉ መሐንዲሶችን እናወጣ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ዛሬ ተጨናፍጓል፡፡ በአጭር ጊዜ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው መሐንዲሶችን እያፈራንና በውጭ አገር ባለሙያዎች ሳይቀር ለመወዳደር ይበቁ ነበር፡፡ ዛሬ እነዚህን ወጣቶች ሜዳ ላይ ቢበተኑ የአገሪቱን ህልም ማጨንገፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አሁን እየተደረገ ያለው ድርድርም አሳዛኝ ነው ብዋል፡፡ ‹‹ፈፅሞ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ መሄደ አልነበረበትም፡፡ ይህ ደግሞ የአመራር ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኔ ወደ ክልል እስከሄድኩበት ዕለት ድረስ ግድቡ 63 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥም ያልቅ ነበር፡፡ ያኔ መቀሌ ከመጣሁ በኋላ ኢንጂነር ስመኘው መጥቶ ተወያይተን ነበር፡፡ እንድታግዘን ብሎኝ ነበር፡፡ እኔም ፍላጎቱ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ግድቡ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ ያን ያህል ድርድር አያስፈልግም ነበር፡፡ የመደራደር አቅማችንም ትልቅ ነበር፡፡ የሰሞኑ ድርድር ግን የመደራደር አቅማችንን ወደ ኋላ የጎተተ ነው፡፡ ለምሳሌ ሱዳን በስንት ትግል በእጃችን አስገብተን አቅማችን ፈርጥሞ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ጭራሽ ሱዳንንም አጥተናታል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ አይኤምኤፍ ብደር ሲሰጥ በድርድሩ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር አገርን ተጋላጭ አድርጓል ያሉት ሊቀመንበሩ፣ ‹‹ይህ ደግሞ የፖሊሲ ቅማችንንም ሊያሳጣን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ በዓሉ በተከበረበት ዕለት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎችና እንግዶች በታደሙበት የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲዮም ውስጥ ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚደረግ ማንኛውም ጥቃት መቆም አለበት፡፡ የአንድ ብሔር የበላይነት ሊኖር አይገባም፤›› ብለዋል፡፡ የብሔር የበላይነት ያሉትን ክልል በግልጽ ባይናገሩም፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ሊቆም ወይም ሊያበቃ ይገባል፤›› ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ከአክሱም ሥልጣኔ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ ታሪክ የሠራና ብሔር ብሔረሰቦችን ለማጎናፀፍ የታገለ መሆኑን ጠቁመው፣ ለኢትዮጵያ እላፊ ታሪክ ያበረከተ ክልል እንደ ሌሎች ክልሎች በተለየ መንገድ ተጠቃሚ ሆኖ አያውቅም ብለዋል፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ እላፊ ያደረገው ይህ የትግራይ ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቃት እየተፈጸመበት ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ለዚህች አገር እላፊ የሰጠ እንጂ ከሌላው የተሻለ ተጠቃሚ ወይም የበለጠ ሆኖ አያውቅም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ይህ እንዳያበቃና በቀጣይነት እንዲጠራጠር ያለ ስሙ ስሙ የተሰጠው ሆኗል፡፡ እላፊ ከከፈለት ከዚህ አገር የተለያዩ ክፍሎች እንዲጠቃና እንዲባረር ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባለፈም ወደ አገራቸው አባረርናቸው ማለትም ተጀምሯል፡፡ ትግራዋይ በማያስፈልገው ተንኮል እንዲጠቃና እንዲጠላ ተደርጓል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
‹‹ያለንበት ጊዜ ፈርተህ የምትኖርበት ወይም የልመና መንገድ የምትከተልበት ሳይሆን፣ በመከባበር መንገድ የምትጓዝበት ነው፡፡ በዚህ ወቅት የማንም ብሔር የበላይነት ተቀባይነት የለውም፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ካልሆነ ግን የትግራይ ሕዝብ ታግሎ ያረጋገጠውን መብት እጁ ላይ እንዳለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከፌዴራሊስት ኃይሎች ጋር ለመሥራት አሁንም ቢሆን ዝግጁ ነን፤›› ያሉት ሊቀመንበሩ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ ይፈጸማል ያሉትን ጥቃት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት በቀሩ ጊዜያት፣ ሊያወግዝ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‹‹በዚህ አጋጣሚ ለሳስብ የምወደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተሰጣችሁ የኮንትራት ጊዜ እየተገባደደ ነው፡፡ ከመበተናችሁ በፊት ታሪክ ሥሩ፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያለውን ጣልቃ ገብነትም ሆነ ትግራይን በተመለከተ በመሪዎች በቅርቡ የተደረጉ ፀረ ሕዝብና ፀረ አገር ንግግሮችን በይፋ ኮንኑ፡፡ ካልሆነ ግን ትግራይ ራሷን የቻለች አገር ነች ብላችሁ ወስኑ፣ አውጁ፣ ወይም የሚደረገውን የሚያርም የማስተካከያ ዕርምጃ ውሰዱ፡፡ ወይም ከእነዚህ አንዱን አድርጉ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ዕለት ፓርላማው በይፋ ሊያወግዛቸውና የእርምት ዕርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል ያሏቸውን ሁለቱን ጉዳዮች (የውጭ መንግሥት ጣልቃ ገብነትና በትግራዋይ ላይ ደርሷል ያሉትን ጥቃት) በተመለከተ ሪፖርተር ማብራሪያ እንዲሰጡበት፣ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በሕዝብ ፊት በይፋ ከመጠየቃቸው በፊት ለምን ለፓርላማው በቀጥታ በአጀንዳ መልክ እንዳላቀረቡ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡
ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ በይፋ መልዕክቱን ለማስተላለፍ የተገደዱት፣ በቅርቡ በኤርትራ ፕሬዚዳንት በወያኔ ወይም በትግራይ ሕዝብ ላይ ጥቃት ባዘለ አስተያየት፣ እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በባሌ ጎባና በተለያዩ ሥፍራዎች በይፋ (ሕወሓትን)ና የትግራይን ሕዝብ ስም በማጥፋት መዝለፋቸውን ተከትሎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የኤርትራ ፕሬዚዳንት በቅርቡ ወያኔ ትጠፋለች፣ ያበቃላታል በማለት ሕዝቡ የመረጠውን ድርጅት መስደቡ በቀጥታ የትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ የኤርትራ መሪ መግለጫ የሚያሳየው ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ሊጠይቁ ይገባቸው ነበር፤›› ብለዋል፡፡
‹‹መንግሥት ይህንን ዝም ማለቱ ደግሞ የራሳችን መንግሥት ከኤርትራ ጋር ተባባሪ በመሆን በትግራይ ላይ ደባ እየሠሩ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን፡፡ ሌላ ምሳሌ ብንመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሱ በባሌ ያደረገውን ንግግር መስማት በቂ ነው፤›› ብለው፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኦሮሚኛ ቋንቋ ለባሌ ሕዝብ አድርገውታል የተባለውን ንግግር ሲሰሙ ለማመን ከብዷቸው እንደነበር የገለጹት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ‹‹ለምን ሰበርናቸው፣ አባረርናቸው በማለት እንደ ጠላት ሊቆጥረን እንደቻለ አልገባኝም?›› ብለዋል፡፡ እኛ ነገሮችን በትዕግሥት ማየት ስለመረጥን እንደ ትግራይ ሕዝብ ተሰባሪ እንዳልሆንን ያውቁታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባሌ ያደረጉት ንግግር አንድ ማሳያ ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጀምሮ ተመሳሳይ ጥቃትና ጥላቻ አዘል ንግግሮች በማድረግ፣ የትግራይን ሕዝብ ለማሸማቀቅ ተሞክሯልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ላይ እየተፈጸመ ነው ያሉት ጥቃት ደግሞ መልኩን እየቀያየረ ከአማራ ክልልም ተመሳሳይ ጥቃት ተሞክሮም ነበረ ብለዋል፡፡ ‹‹ግን እኛ በፅናትና በትዕግሥት እያመከንን ስለቆየን እንጂ፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ለአብነት ወደ ትግራይ የሚያስገቡ መንገዶች ሪአማራ ክልል ከሁለት ዓመት በላይ ተዘግተው ሲቆዩ፣ የፌዴራል መንግሥት ዝም ማለቱን አንስተው ወቅሰዋል፡፡ ‹‹በመንገዶቹ መዘጋትን የአማራ ክልል ተባባሪ ነው ማለት ባንችልም፣ አመራሩ ውስጥ ይህ አስተሳሰብ ያላቸው ኃላፊዎች ግን አሉ፤›› ብለዋል፡፡ ከአማራ በኩል ቀድሞ የነበረው ውጥረት ከአዲስ አመራር መምጣት ጋር ተያይዞ በመጠኑ ረገብ ማለቱን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን የተለያዩ የጎበዝ አለቆች በትግራይ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ሲሞክሩ ቢስተዋልም ወዲያው እየጠፉም ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ
በኢትዮጵያና በኤርትራ ዳግም የተጀመረውን አዲስ ግንኙነት በመለከተም አስተያየት የሰጡት የሕወሓት ሊቀመንበር፣ ግንኙነቱ ተቋማዊ መሆን አልቻለም ብለዋል፡፡ ሲጀመር በ2010 ዓ.ም. የኢሕአደግ ግምገማ ወቅት ራሳቸው የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ዕልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ቀድመው ማንሳታቸውንና በተለይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን በቅርቡ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ባድመን ላለመረከብ እንቅፋት የሆነባቸው ሕወሓት ነው ማለታቸውን መሠረት ቢስ ክስ ነው ብለው፣ ሕወሓት በባድመ ጉዳይ መንግሥት ከያዘው አቋም የተለየ አቋም እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈታ መሆኑን፣ የትግራይ መንግሥት የሚሰጠውም ወይም የሚከለክለው ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ ችግሩ ሁለቱ መንግሥታት የአገሮቹን ግንኙነት በተቋማዊ መንገድ ማሸጋገር አለመቻላቸው መሆኑን ተችተው፣ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከማለት ይልቅ፣ የኢሳያሳና የዓብይ ግንኙነት ብቻ ጎልቶ የወጣበት፤›› ነው ብለዋል፡፡
የባድመ ጉዳይን መወሰን የሚችለው በቀዳሚነት የፌዴራል መንግሥት ይሁን እንጂ፣ በጉዳይ ላይ በአግባቡ ውሳኔ ካልተሰጠ የችግሩ ተሸካሚ የትግራይ የክልሉ ሕዝብ መሆኑን፣ መንግሥት ይህን ጉዳይ ተቋማዊ በሆነ መንገድ መፍታት እንዳለበት ፍላጎታቸው መሆኑን፣ ነገር ግን ድጋሚ ከኤርትራ ጋር ወደ ውጊያ ሊከት እንደማይችል ተደርጎ ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱ መሪዎች በኩል የአገሮቹን ግንኙነት ወደ ተቋም ከማሸጋገር ይልቅ፣ ‹‹ፀረ ሕወሓትና ፀረ ትግራይ ሴራቸውን እያሳዩን ነው፤›› በማለት ወቅሰዋል፡፡
የመቀሌው ኤርፖርት አጋች ታጋች ድራማ በተመለከተ
ባለፈው ዓመት አጋጥሞ ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮች ታፎነው በቆዩት የመቀሌ አሉላ አባ ነጋ ኤርፖርት በተመለከተ፣ በትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ታግተዋል ስለተባለው የፌዴራል ፖሊስ ጉዳይ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ቁጥራቸው 45 የሚደርሱ ከተለያዩ የፀጥታ ተቋማት ተወጣጥተው የተላኩ ልዩ የፌዴራል ፖሊስ ኃይል አባላት፣ ማንነታቸው ያልተገለጸ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ከመቀሌ ለመያዝ ተልከው እንደነበር በወቅቱ ተሰምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ማብራሪያ በክልሉም ሆነ በፌዴራል ፖሊስ ሳይሰጥበት ተዳፍኖ ቆይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) በመግለጫቸው ተላኩ የተባሉ የፌዴራል ልዩ ኃይል አባላት ኤርፖርት ከመድረሳቸው በፊት የክልሉ ደኅንነት መረጃ እንደነበረው፣ መቀሌ ሲደርሱ ከተሳፈሩበት አውሮፕላን ሳይወርዱ መከበባቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹በአየር ኃይል አውሮፕላን ነበር የመጡት፣ በቅድሚያ እንደሚመጡ ለክልሉ መንግሥት አላሳወቁም ነበር፡፡ አውሮፕላኑ እንዳረፈ ወዲያው ከበብናቸው፡፡ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አሳሰብናቸው፡፡ ዕርምጃ እንደምንወስድባቸው ካሳወቅን በኋላ ምክትል ኮማንደሩንና ሌሎች ሁለት ሰዎች ብቻ አስረን ጠየቅናቸው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በምርመራ ወቅት በተገኘው መረጃ መሠረት ልዩ ኃይሉ የእሴት ሰንሰለቱን በተበጣጠሰ ሁኔታ ከተለያዩ ዩኒቶች ተወጣቶ አንዱ ፖሊስ ሌላውን እንዳያውቅ ተደርጎ የተዋቀረ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር አንድም ከትግራይ ክልል የተመለመለ ፖሊስ እንዳይኖር ተደርጎ የተዋቀረ ኃይል ነበር፡፡ አጠቃላይ አወቃቀሩን ስንመለከት የአመራሩን ብስለት ጉድለት የሚያሳይ የልጅ ጨዋታ የሚመስል ነገር ነበር፡፡ እኛ በልምድ በምናውቀው በትክክለኛና በተቋማዊ አሠራር መሠረት ለአንድ ተግባር የፀጥታ አካል ከአንድ የሆነ ዩኒት መርጠህ ነው የምትልከው፡፡ በዚህ ግን የሆነው አሠራሩ ሕገወጥና ኢተቋማዊ ነበር፡፡ ይህን ያደረጉት ሚስጥር እንዳይወጣ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደውለው ማብራርያ ጠይቀው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተላከው ልዩ ኃይል የሚያውቁት ጉዳይ እንደልነበር ገልጸውልኝ ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን እሳቸው የማያውቁት ኃይል ተልኳል ብለው ለማመን እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ቢያንስ ቢያንስ የአገሪቱ መከላከያ ኃይል የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ሆነው ሳለ፣ ይህ ቡድን የአየር ኃይል አንቶኖቭ አውሮፕላን አስነስቶ ሲመጣ፣ እኔ አላውቅም ማለታቸው ራሱ ያስገርማል፤›› በማለት አክለው ገልጸዋል፡፡
ብልፅግና የኢሕአዴግ ወራሽ?
ኢሕአዴግ አራት የግንባሩን መሥራች ድርጅቶች አጣምሮ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ሦስት ድፍን አሠርታት ሊሞላው አንድ ዓመት ብቻ ሲቀረው ነበር፣ ባለፈው ወር በይፋ ፈርሶ አዲሱ ውህድ ፓርቲ ወይም የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ የተመሠረተው፡፡ በ29 ዓመቱ አንጋፋው ግንባር መፍረስ የሕወሓትና የሦስቱ አባል ድርጅቶች ፍቺ የተፈጸመበት ነው፡፡
ይህንን አስመልክቶ በሕወሓትና በአዲሱ ውህድ ፓርቲ ከዚህ በኋላ ስለሚኖረው ግንኙነት በተመለከተ ሪፖርተር የእሳቸውን አስተያየት ጠይቆ ነበር፡፡ በምላሻቸውም ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት አብራርተዋል፡፡
ፍቺውን ሕወሓት ፈልጎት ባይፈጽምም ተቀብሎት በራሱ የፖለቲካ ትግሉን እንደሚቀጥል፣ ላለፉት 45 ዓመታት ሲታገልበት የቆየውን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ማስከበር ጉዳይ ከሌሎች ማናቸውም የፌዴራሊስት ኃይሎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በመጪው ነሐሴ በሚደረገው ምርጫ ሕወሓት በትግራይ ሙሉ በሙሉ እንደሚያሸንፍ ጥርጣሬ እንደሌለው በመግለጽ፣ ብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ሥልጣንን ቢያሸነፍ እንኳ ሁለቱ ፓርቲዎች ባገኙት ሥልጣን መሠረት የየድርሻቸውን ማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት (ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ) ያለ በመሆኑ፣ ምንም ችግር እንደማይኖር ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ ይህ ዓይነት ልምድ ከዚህ በፊት በተግባር ታይቶ ባያውቅም፣ በሌላው ዓለም እንዳለው ዓይነት የአስተዳደር ተግባር ይከናወናል ብለዋል፡፡ ለአብነትም በህንድ ክልል የሚመራ የኮሙዩኒስት ፓርቲ መኖሩን በመጠቆም፣ ሕወሓት ክልሉን ከፌዴራል መንግሥት ጋር በማያጋጭ መንገድ የሚሠራበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ከኢሕአዴግ መፍረስ በኋላ በሕወሓትና በብልፅግና መካከል የተጀመረ አዲስ ግንኙነት ወይም ውይይት ስለመኖሩ ሪፖርተር ላነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ ሁለቱ ድርጅቶች ኮሚቴ በማቋቋም ለመነጋገር መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዚህ ጉዳይ ላይ ከወራት በፊት በስልክ እንዳናገሯቸው በማስታወስ፣ የክልሉ መንግሥት በኮሚቴ አባልነት ከብልፅግና ጋር የሚወያዩ ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን መመደቡን ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) አመልክተዋል፡፡
‹‹የመረጥናቸውን አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደውዬ ነግሬዋለሁ፡፡ እሱ እንዲያውም ረስቶት እንደነበረና እንደሚያሳውቀኝ ገልጾልኛል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ የኮሚቴዎቹን ውይይት በተመለከተ ብልፅግና ፓርቲ የራሱን አባላት ባሳወቀበት ጊዜ እንነጋገራለን ሲሉ አክለዋል፡፡ በዚሁ መግለጫቸውም ብልፅግና የኢሕአዴግ ወራሽ እንደሆነ መግለጹን በተመለከተ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የሕወሓት ሊቀመንበር፣ ‹‹ብልፅግና የኢሕአዴግ ወራሽ ነው የሚባለው አደረጃጀቱን እንጂ፣ የመንግሥት ሥልጣኑን ነው ተብሎ ሊገለጽ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡
ምናልባት በዚህ ጉዳይ ክርክር፣ የአካሄድ፣ የሕግና አደረጃጀት ጉዳይ ማንሳት ቢቻልም ለጊዜው ለመንግሥት የሥልጣን ጊዜ የቀሩት ጥቂት ወራት ብቻ ስለሆኑ ብዙም የሚያሳስብ ጉዳይ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ሕወሓት መጪው ምርጫ በነሐሴም ሆነ በማንኛውም ሰዓት እንዲወሰን ብቻ ነበር ፍላጎቱ ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ቀደም ብሎ ሕወሓት አቋሙን ሲገልጽ መቆየቱን በመጥቀስ፣ ምርጫው በምንም ዓይነት ሁኔታም ሆነ ዝግጅት መካሄድ እንዳለበት ብቻ አሳስበዋል፡፡ እንደ ሕወሓት እምነትም ምርጫው በዚህ ዓመት የማይካሄድ ከሆነ ግን፣ አገሪቱ መውጫ የሌለው ችግር ውስጥ እንደምትገባ አስታውቀዋል፡፡