የአማራ ክልል ምክር ቤት አዲስ ርዕሰ መስተዳድር ሰየመ፡፡
ባሕር ዳር፡ የካቲት 29/2011 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለፓርቲያቸው መልቀቂያ ማቅረባቸውንና አዴፓ መልቀቂያውን መቀበሉን ተከትሎ ለምክር ቤቱ የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
የርዕሰ መስተዳድር ለውጥ እንዲደረግ የቀረበለትን ጥያቄ የተቀበለው የአማራ ክልል ምክር ቤት በአዴፓ በዕጩነት የቀረቡለትን ዶክተር አምባቸው መኮንን ሲሳይን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሰይሟል፡፡
ዶክተር አምባቸው መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት አማካሪ ሚኒስር ናቸው፡፡
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ‹‹ታላቁን የአማራ ሕዝብ ለመምራት ዕድል የሰጠኝን ፓርቲዬን አመሠግናለሁ፤ በስልጣን ዘመኔ በሰጠኋቸው ውሳኔዎች ያስከፋኋችሁ ካላችሁ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ወኔና ጉልበት ሆኖኝ የኖረውን የአማራ ሕዝብ አመሠግናለሁ፤ ለአዲሱ ርዕሰ መስተዳድርም መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ›› ብለዋል በመሰናበቻ ንግግራቸው፡፡