በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ውጥረትን አንግሷል። ይህን ብቻ አይደለም በቅርቡ በክልሉ ውስጥ ለሚፈጸሙ ግድያዎች እና ዘረፋዎች መንግሥት ኦነግን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።
በቅርቡ የክልሉ ፖሊስ እና ባለስልጣናት በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ኦነግን የአከባቢው አስተዳደሮችን ይገድላል፣ ጦር መሳሪያ ይዘርፋል እንዲሁም ሚሊሻዎችን ትጥቅ ያስፈታል ሲሉ ከሰዋል።
ኩምሳ ዲሪባ ወይም በትግል ስሙ ጃል መሮ ተብሎ የሚታወቀው በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ጦር አዛዥ ነው።
ጃል መሮ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሳው የኦነግ ሠራዊት ዘንድ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ብቻም ሳይሆን አንዳንዶች ከሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ እዝ ነጻ ሆኖ በራሱ የሚንቀሳቀስ ቡድንን የሚመራ እንደሆነ ይነገርለታል።
ቢቢሲም በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ሁኔታ እና ከኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስላለው ግነኙነት ከጃል መሮ ቃለምልልስ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው የኦነግ ጦር ተልዕኮው ምንድነው?
ጃል መሮ፡ ኦነግ የራሱ የሆነ ፍላጎት ወይም ተልዕኮ የለውም። ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትን ነው የሚያስጠብቀው። ጦሩም የኦነግን ተልዕኮ ነው የሚወጣው። ይሄው ነው።
ቢቢሲ፡ የኦነግን ጦር ወደ ካምፕ በማስገባቱ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድነው?
ጃል መሮ፡ በቀላል ቋንቋ ላስረዳህ። በአንድ ቤተሰብ አባለት ውስጥ አባት፣ እናት እና ልጆች ይኖራሉ። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ወላጆች ማለትም እናት እና አባት እስካሉ ድረስ ቤተሰባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠት የሚኖርባቸው እነርሱ ናቸው፤ ልጆች አይደሉም። የኦነግ ጦር ወደ ካምፕ ይግባ ወይም አይግባ በሚለው ላይም የኦነግ አጠቃላይ አመራሮች የሚወስኑትን ነው እኛ የምናስፈጽመው። ወደ ካምፕ እንገባለን ወይም አንገባም የሚለውን እኔ ልመልስ አልችልም።
ቢቢሲ፡ በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ጦር ከሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ ትዕዛዝ ውጪ ነው ይባላል። ከአቶ ዳውድ ቁጥጥር ውጪ ናችሁ?
ጃል መሮ፡ በምዕራብ ዞን የሚገኘውም ይሁን በሌሎች ዞኖች ውስጥ የሚገኘው የኦነግ ሥራዊት በሙሉ ተጠሪነቱ፣ የሚመራውም፣ ትዕዛዝ የሚቀበለውም ከኦነግ ሊቀመንበር ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ነው። አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር ናቸው። የኦነግ ጦር ደግሞ ካሉት የኦነግ ዘርፎች አንዱ ነው። ስለዚህ ተጠሪነቱም ለሊቀመንበሩ ነው። በአጭሩ ይሄው ነው። ከዚህ የተለየ ነገር የለም።
ቢቢሲ፡ በቅርቡ ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር በምዕራብ ኦሮሚያ ተገናኝታችሁ እንደተወያያችሁ ተሰምቷል። የውይይታችሁ ርዕሰ ጉዳይ ምን ነበር?
ጃል መሮ፡ አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር እና የጦር የበላይ አዛዥ ናቸው። ከእሳቸው ጋር ብዙ ጉዳዮች ያገናኙናል። ብዙ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን። ውይይታችንም አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ አይደለም። በቋሚነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። የተወያየንበትን ርዕሰ ጉዳይ ማወቅ ካሻህ ግን እሳቸውን ደውለህ ጠይቅ።
ቢቢሲ፡ ሰሞኑን እርሶ ለኦነግ ወታደሮች ያስተላለፉት መልዕክት እንደሆነ የተነገረ ደምጽ በርካቶች በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ሲቀባበሉት ነበረ። ድምፁ የእርስዎ ነው?
ጃል መሮ፡ ስለ ጉዳዩ የማውቀው ጉዳይ የለም። እስቲ ነገረኝ፤ ምንድነው እሱ?
ቢቢሲ፡ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሰዎች ሲጋሩት የነበረው ወደ 48 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው የእርስዎ ነው በተባለ ደምጽ፤ ‘ትጥቅ ያስታጠቀንም ሆነ የሚያስፈታን የለም’ የሚል ይዘት ያለው መልዕክት ነው የተላለፈበት።
ጃል መሮ፡ እንዲህ ባለ ጉዳይ ላይ ድምጽ ቀርጸን አናሰራጭም። ይህ የምትለው ድምጽ የት እንደተቀረጸ፣ ማን እንደቀረጸው እና እኔ መሆኔ መረጋገጥ አለበት።
ቢቢሲ፡ የቤንሻንጉል ጉሙዝ አስተዳዳሪዎችም እንዲሁም በቅርቡ አቶ ለማ መገርሳ ለካማሼ ዞን አስተዳደሪዎች ግድያ ተጠያቂው የኦነግ ጦር ነው ብለዋል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምነድነው?
Image copyrightFACEBOOK
ጃል መሮ፡ በዚህ አካባቢ የታጠቀ ኃይል በርካታ ነው። የታጠቀ የመንግሥት አካል፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ታጣቂዎች እንዲሁም የኦነግ ታጣቂዎች በስፍራው ይንቀሳቀሳለሁ። ይህ ሁሉ ታጣቂ ቡድን ባለበት ኦነግ ላይ ብቻ ጣት መቀሰር አይቻልም፤ ትክክልም አይደለም። ገለልተኛ የሆነ አጣሪ አካል ወንጀሉን የፈጸመውን ማጣራት አለበት።
ቢቢሲ፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኦነግ በምዕራብ ኦሮሚያ የመንግሥት ሥርዓትን ይንዳል፣ ጦር መሳሪያዎችን ይዘርፋል የሚሉ በርካታ ክሶችን ይሰነዝራል። እርስዎ ምን ይላሉ?
ጃል መሮ፡ ከዚህ ቀደም ጦርነት ላይ ነበርን። ስንዋጋ ነበረ። የሚወጋንን ጦር አስተዳደራዊ ሥርዓቱን፣ ፖሊስን፣ ሚሊሻውን መበጣጠስ ደግሞ ግድ ነው። የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከደረስን በኋላ ኦነግ በራሱ ተነሳሽነት መንግሥት ላይ ተኩስ ከፍቶ አያውቅም፤ አጸፋዊ እርምጃ ካልወሰድን በቀር።
ይህ ሁሉ ክስ ግን ሃሰተኛ ነው። መንግሥት ይህን ክስ የሚያቀርበው በዚህ አካባቢ ላይ ጦሩን በማዝመት ጦርነት ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት ሲያከናውን ነው እንጂ ኦነግ ያፈረሰው የመንግሥት ሥርዓት የለም፤ የዘረፈውም የጦር መሳሪያ የለም። እንደውም የኦነግ ጦር ሥነ-ምግባር በተሞላበት መልኩ ተቆጣጥሮ ከያዘው ስፍራ አልተንቀሳቀሰም።
ቢቢሲ፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ኦነግ ተቆጣጥሬያለሁ የሚለው መሬት የትኛውን ነው?
ጃል መሮ፡ እሱን የምዕራብ ኦሮሚያ ህዝብን መጠየቅ ትችላለህ።
ቢቢሲ፡ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ከተሰማራው የሃገር መከላከያ ጦር ጋር የተፈጠረውን ግጭት ይንገሩኝ እስቲ
ጃል መሮ፡ የመጣብንን ጠላት መመከት እና ወደ መጣበት የመመለስ ችሎታውም ሆነ አቅሙ አለን። መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ ነን። አሁንም ቢሆን የመጣብንን ኃይል እየተከላከልን እንገኛለን። በዚህ መካከል ግን ችግር ውስጥ እየገባ ያለው እና እየተሰቃየ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ነው። የመንግሥት ጦር ውስጥም ያሉት ወታደሮች ህጻናት እና የደሃ እናት ልጆች ናቸው።
ይህ ግጭት ግን ለሁለቱም [ኦነግ እና መንግሥት] ወገን የሚያስገኘው ጥቅም የለም። በዚያም ሆነ በዚህ እየተጎደ ያለው ኦሮሞው ነው።
ቢቢሲ፡ ለዚህ መፍትሄው ምንድነው?
ጃል መሮ፡ የግል የፖለቲካ ጥቅምን ለማስጠበቅ ከማሴር ይልቅ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ብናስቀድም፤ ይህ ሁሉ ችግር በአንድ ለሊት መፍትሄ ያገኛል። የግል የፖለቲካ ጥቅም ከህዝብ ፍላጎት ካስቀደምን ግን ለዚህ ችግር መቼም ቢሆን መፍትሄ አይገኝም።
ቢቢሲ፡ በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ ኦነግ ሰላማዊ ትግል ለማካሄደ ወደ ሃገር ውስጥ ከገባ በኋላ ጦር እንደ አዲስ በመመልመል እያሰለጠነ ይገኛል ይባላል። ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ጃል መሮ፡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከታወጀ በኋላ የተካሄደ ምንም አይነት ስልጠና የለም።
• ዐቢይ አሕመድ ለምን ወደ አምቦ አቀኑ?
ቢቢሲ፡ ስለ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ምን ያስባሉ?
ጃል መሮ፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም።
ቢቢሲ፡ ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ለውጦች መጥተዋል። እርስዎ የኦሮሞ ህዝብ ነጻነቱን አግኝቷል ብለው ያምናሉ? ወይም ኦሮሞ ነጻነቱን የሚጎናጸፈው መቼ ነው?
ጃል መሮ፡ እኔ እንደ አንድ ግለሰብ ነጻነቴን አላገኘሁም። ህዝቡም የእራሱን መልስ መስጠት ይችላል።