ከትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ
======================================
ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ በነፃነት የመንቀሳቀስ እንዲሁም በመረጡት ኣከባቢ የመኖር እና ሃብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው መሆኑ ከተረጋገጠ ቆይቷል፡፡ የፌደራልና የክልል መንግስትም ይህ ህገ-መንግስታዊ የዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ ኣስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉና ጥሰት ሲያጋጥም ደግሞ ኣስቸዃይ መፍትሔ በመስጠት በእንደዚህ ዓይነት የጥፋት ድርጊት ለሚሳተፉ ኣካላት ህግ ፊት ማቅረብ ደግሞ ህግ-መንግስታዊ ግዴታ ኣለባቸው፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ኣመታት በተለያዩ የኣገራችን ክፍሎች የተለያዩ ብሄረሰብ ተወላጆች ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ በህይወት እና ንብረታቸው ላይ የሚደርስ የጥቃት ዜና መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በትግራይ ተወላጆችም ተመሳሳይ በደል መፈፀሙን የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም በኣማራ ክልል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የትግራይ ተወላጆች ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድና በተደጋጋሚ ህገ-መንግስታዊ ጥሰት እየተፈፀመ ይገኛል፡፡ የየኣከባቢው ህዝብ አደጋውን ለመቀነሰ ጥረት ባያደርግ ንሮ ከዚህ የከፋ ጥፋት ሊደርስ ይችል እንደነበረ ይታመናል፡፡ የተለያዩ ኣጀንዳዎች በመቅረፅ በትግራይ ህዝብ ሰላምና ድህንነት በማወክ ዙርያ የሚደረግ ዘመቻ ኣሁንም ሳያቋርጥ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ እጅን ከማስገባት በተጨማሪ ከትግራይ ጋር የሚያስተሳስሩ መንገዶች በመዝጋት እና የትግራይን መሬት በሃይል ለመውረር መፈለግ የመሳሰሉ ያረጁና ሃሏ ቀር ኣስተሳሰቦችና ክፉ ተግባራትም እየታዩ ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኣሁንም ትላንት በመተማና ሌሎች አከባቢዎች ተመሳሳይ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ ችግር በተፈጠረባቸው ኣከባቢዎች ኣንዳንድ የኣማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ኣስቀድመው በማንቀሳቀስ የደረሰውን ግፍ እንዲፈፀም ኣመራር የሰጡ መሆኑን ታውቆ ባስቸኳይ ወደ ህግ ሊቀርቡ ይገባል፡፡ ሰዎች ለማህበራዊ ልማት ሊተጉ ሲገባ ለጥፋት እንቅልፍ ኣጥተው ሌተቀን ሲሰሩ ማየት ኣሳዛኝ ሲሆን ጥፋትን በጥፋት መመለሰ ግን ቀላል መሆኑን ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የትግራይ ህዝብና መንግስት ደግሞ ለጥፋት ሳይሆን ለጋራ ልማትና ሰላም የቆመ በመሆኑ የሁለቱን ህዝብ ወንድማማችነት የሚያጠናክሩ እንጂ የሚያፈርሱ ስራዎች የማንሰራ መሆኑን አሁንም በድጋሜ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ይህ ማለት ግን በህዝባችን ላይ የሚፈፀሙ የጥፋት ተግባሮች ኣይተን እንዳላየን እንሆናለን ማለት ኣይደለም፡፡ በህዝባችን ንብረትና ህይወት ላይ ጉዳት ያደረሱ በሙሉ እንደ ክልል መንግስት በህግ እንዲጠየቁ ጥረት የምናደርግ ይሆናል፡፡ የኣማራ ክልል እና የፌደራል መንግስትም ህገ-መንግስቱን ያለ ማቋረጥ በተደጋጋሚ በሚጥሱ ኣካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡ ለዘመናት ኣብረው የነበሩና በብዙ መንገድ የተሳሰሩትን ህዝቦች ኣንድነታቸውና ወዳጅነታቸው ኣጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማስቀጠል ይልቅ ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ ጥቃት ሲፈፀም ማየት የሚያሳዝን እና የሚሳፍር ድርጊት ነው፡፡ የኣማራ ክልል ህዝብና መንግስት እንዲሁም የፈደራል መንግስት ይህ ማንነት መሰረት ኣድርጎ እየተፈፀመ ያለውን በደል ኣጥብቆ በማወገዝ ኣስቸኳይ ምላሽ በመስጠት የዜጎችን ደህንነት እንዲጠበቅ፣ የወደመ ንብረታቸው እንዲተካና በተለያዩ ግዚያት በህዝብ ላይ ግፍ የሚያደርሱትን ወንጀለኞች በሙሉ እንዲሁም መንግስት በቅርብ በምህረት ለቋቸው ሲያበቃ በወንጀል ተግባር ላይ የተሰማርቱን ጨምሮ ወደ ህግ እንዲቀርቡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በመጨረሻም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት እና ግፍ ለተፈፀመባቸው ሁሉ የተሰማውን ሓዘን በመግለፅ የዚህ ኣስነዋሪ ተግባር ሰለባ ለሆኑ ቤተሰብና ኣካላት በትግራይ ህዝብ እና መንግስት ስም መፅናናትን ይመኛል፡፡
የትግራይ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ
ጥቅምት 27/2011 ዓ.ም