የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅት የሆነው ኦዴፓ (ODP) በእነ ሌንጮ ለታ ከሚመራው ኦዴግ (ODF) ጋር ዛሬ ህጋዊ ውህደት ፈጸመ። ቀደም ሲል ኤርትራ ከነበረው ኦነግ ተነጥለው ሌሎች ድርጅቶች መስርተው እየታግልን ነው ሲሉ ከነበሩት ከእነ ከማል ገልቹ ጋር ያልታወጀ ውህደት ማድረጋቸው ይታወቃል። ኣዴፓም (የድሮ ብኣዴን) በኤርትራ ነበርኩ ከሚለው ከኣዴን (ከኣርበኞች የወጣ) ጋር መዋሃዱ ይታወሳል። ሌላው የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅት ደግሞ ደኢህዴን ነበር (ነበር ለበል እንጂ) ደግሞ በሲዳማ፣ ወላይታ ሶዶ፣ ከፋ፣ ጉራጌ እና ስልጤ ተከፋፍሎ የየራሱ ክልል የመመሰረት ውሳኔ በየዞኑ ወስኖ ብትንትኑ በመውጣት ላይ ይገኛል። የድርጅቱ ሊመንበርና የሰላም ሚኒስተሯ ወሮ ሙፍሪያት በግምባሩ (ኢህዴግ) ሆነው ማንን እንደሚወክሉ እና የየትኛውን ቡድን ፍላጎት ለሟሟላት እንደሚሰሩ ማወቅ ኣስቸጋሪ ቢሆንም ይህ ጥያቄ መነሳት ያለበት ኣሁን በመበታተን ላይ ካሉት የኣመራር ኣባላትና የድርጅቱ ምክርቤት ነው። በእርግጥ የሚያለፍ ጉዳይ ኣይሆንም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትጥቅ ትግሉ ሂደት እጅግ ትልቅ መስዋእት በመክፈል ደርግን ላይመለስ በመገርስስ፣ ኢህኣዴግን በመመስረት እና ኣዲስቷን ኢትዮጵያ በመገንባት የኣንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ህወሓት ደግሞ ወይ እንደ ሌሎቹ ኣባል ድርጅቶች ያደረጉት ኣይነት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ውህደት ሳይፈጥር ኣሊያም የግምባሩ ኣባል ድርጅቶች እያደረጉት ስላለው ሌላ ውህደት ምንም ኣይነት ጥያቄም ሳያነሳ በተግባር በፈረሰው ግምባር ውስጥ መቀጠል የመረጠ ይመስላል። ለምን ይሆን? መገመት ያስቸግራል።
ኢህኣዴግን በሊቀመንበርነት እየመሩ ያሉት ኣብይ ኣህመድ እና ተቃዋሚ ድርጅቶች ሰሞኑን ባደረጉት የምክክር መድረክ የለፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት እንደ ችግር በመታየቱ ድርጅቶች ውህደት በመፈጸም ኣሁን ያለው ብዛት ወደ ሶስትና ኣራት ድርጅቶች ቢወርድ ለኣገሪቱና ለፖለቲካ ምህዳሩ እንደሚጠቅም በኣፅኖት ሃሳብ ቀርበዋል። የወቅቱ የጎራ መደባለልቅና የኢህኣዴግ እጣ ፈንታ ኣስመልክቶ ነሃሴ ወር ላይ በፃፍኩዋት ኣንድ ኣጠር ያለች ፅሁፍ እንደሚከተለው ብየ ነበር:
‘’ውሎ ኣድሮ ሁሉም የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች እስከ ኣሁን የሄዱበት መንገድ እና በየጎራቸው የፈጠሩትን መርህ ኣልባ ግኑኝነት ያልተጠበቀ ውጤት ኣስከትሎ ኣዲስ ኣሰላለፍና ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ትርምሱ ይቀጥላል። ኣሁን ባለው ሁኔታ ረጅም ርቀት እንደማይሄድ ከወዲሁ በርካታ ምልክቶች እያየን ነው። በትክክል ለመተንበይ በሚያስቸግር የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ሆነንም ቢሆን የኢህኣዴግ ቀጣይ ጉዞ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ኣይከብድም።’’ ይላል።
ወረድ ብሎሞ ‘’ተስፋ የሚደረገውና መሆን ያለበት ሁሉም የኢህኣዴግ ድርጅቶች ቆም ብለው ራሳቸውን ከኣባል ድርጅቶች ጋር ማወዳደርን ትተው ውስጣዊ የፖለቲካ ኣቋማቸውን ቢፈተሹና የዓላማ ኣንድነት እና መርህ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ህብረትና ኣቅጣጫ ቢከተሉ ለኣገርም ሆነ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝብ እንደሚጠቅም ኣጠያያቂ ኣይሆንም።’’ ይህ ግን የሚሆን ሆኖ ኣልተገኘም። ራሳቸውን ከመፈተሽና ካማስተካከል ይልቅ ኣንዱ ኣንደኛውን በማጥቆርና በማጥላላት ክህብረቱ ውጭ ሌላ ውህደት ለመፈጸም መርጠዋል። ያውም በዓላማ ከመቃረን በላይ በትጥቅ ትግል ሲፈልጉዋቸው ከነበሩ ድርጅቶች ጋርም ጭምር።
እዚህ ላይ ግን ‘’ኣባል ድርጅቶቹ ሲከተሉት ከነበሩት የኢህኣዴግ የጋራ የፖለቲካ ፕሮግራም ውጭ ለመሄድ ከፈለጉም እንደ ከህደት ሳይሆን እንደ መብታቸው መታየት ይኖርበታል። ሲጀምር በሁሉም ነገር መቶ ለመቶ ተስማምተው ኣልነበረም ግንባር የፈጠሩት። ሲቀጥል ጊዜ የሚወልዳቸው ኣዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ኣመለካከትና ስልት የመቀየር ፍላጎትች ልዩነት እንደሚፈጠሩ ከግምት ውስጥ ማስገባት የግድ ይላል። የፖለቲካ ኣቅጣጫ ለመቀየር ግን በሌሎች፣ ያውም ኣብሮህ በኣንድ ፕሮግራም ጥላ ስር አየታገለ ባለው ድርጅትና እሱ በሚመራው ህዝብ ላይ የፖለቲካ ሴራ መጎንጎን እና ዘረኝነት እንደ መሳሪያ መጠቀም የግድ ኣይልም። ለሁሉም ኣይጠቅምና።’’ በማለት ምክሬን ለግሻለሁ።
በመጨረሻም ‘’የኢህኣዴግ ኣባል ድርጅቶች ኣሁን እየታየ ያለውን የተዘበራረቀ የፖለቲካ ኣቋም ኣጥርተው ግንባሩም በይፋ ኣፍርሰው ሁሉም ወደየ ጎራቸው የሚቀላቀሉበት ጊዜ ሩቅ ኣይሆንም። እስከ ኣሁን በኣሰራር ያፈረሱት ቢሆንም በኢህኣዴግ ምክንያት የመጣውን ስልጣን ድልድዩ እስኪሻገሩበት ድረስ ግንባሩን በይፋ ማፍረስ ኣልተፈለገም። በእርግጥ ጠ/ሚንስትሩ ኣንዴ ‘’ኢህኣዴግ የትም የለም’’ ሲሉ ኣስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ‘’ኢህኣዴግ ከምን ጊዜ በላይ ጠንካራ ሆነዋል’’ በማለት እርስ በርሱ የሚቃረን ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል።’’ የሆነ ሆኖ በኣዋጅ ኣልተነገርም ካልሆነ በስተቀር ግምባሩ በተግባር ፈርሰዋል። በመሆኑም ኣባል ድርጅቶችም ህጋዊ ፍቺ ኣድርገው፣ ያላቸው ንብረት እና ሰነድ ተካፋፍለው ወደየ ጎራቸው በመዋሃድ ኣሊያም ብግል ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት ቢያደርጉ ይመከራል።
በዚህ ጸሃፊ ሁኔታን መሠረት ያደረገ ግምት፣ ድርጅቶቹ የሚከተሉትን የኢኮኖሚና የማህበረ ሰብ ልማትን በተመለከተ ለስሙ ካልሆነ በስተቀር የፊልሚያቸው ዋና ኣጀንዳ የሚያጠነጥነው ህወሓት ኢህኣዴግ የሰራትን ፌደራላዊት ኢትዮጵያን ኣፍርሶ የመስራት ጉዳይ ወይም በትንሽ ለውጥ ማስቀጠል ስለሚሆን ቀጣዩን የስርኣት ግንባትን በሚመለከት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች በሁለት ጎራ መከፈላቸው ኣይቀርም። በዋናነት የፌደራል ስርኣት የሚከትሉ ድርጅቶች ስብስብ እና ኣሃዳዊ ስርኣትን መከተል የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ በተላየዩ ፖለቲካዊና የኣቋም መዋዥቅ ወይም እርግጠኛ ያለመሆን እንዲሁም ግላዊ ምክንያቶች በሁለቱም ጎራ የማይቀላቀል ሌላ ስብስብ ወይም በተናጥል የሚቀር መኖሩ ኣይቀሬ ነው።
በኣጭሩ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በእነዚህ ሁለት ጎራዎች (ፌደራልሲት እና ኣሃዳዊ ስርኣትን የሚሉ) መካከል በሚደርግ ፍትጊያ ሲሆን ሂደቱ በሰላማዊ ከሆነ ኣገራችን የማስቀጠል ዕድል ይኖራል በተቃራኒው ከሆነ ደግሞ ኣስከፊ እና ተመልሶ ሊጠገን የማይችል የመበተን ኣደጋ ሊያጋጥም ይችላል። ምርጫው የድርጅቶቹና ተከታዮቻቸው ነው።
ቸር ያሰማን
ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ
ታህሳስ 2011 ዓ/ም
ከላይ የተጠቀሰው ፅሁፍ ለማንበብ ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይከፈቱ።
http://www.aigaforum.com/amharic-article-2018/eprdf-and-political-mixup.htm