የፖለቲካችን ኬሚስትሪው የት ነው?
አዲስ አበባ የኔ ናት አይደለችም ፣ኢትዮጵያ የፈጠራት የኔ ብሔር ነው አይደለም ፣እኔ ብዙ ነኝ አንተ —-፣እኔ ሲፈጥረኝ ኩሩ አንተ—–፣ኢትዮጵያ እንጂ ብሔር የለም ስለሆነም አንተም የለህም አለሁ፣ዋናው ችግራችን ባንዴራ ነው።የማን የኔ ያንተ፣አይ አይደለም ዋናው ችግሩ የክልላችን ድንበር ነው።አይ ድንበር የለም ወሰን ነው አይደለም።ዋና ችግር ህገ መንግስቱ ነው። አይደለም ፌደራሊም ነው፣የአንድነት ኃይሎች፣የመገንጠል ኃይሎች፣ የፌደራሊዝም ኃይሎች፣ላኪና ተላላኪ፣የበላይነት የበታችነት፣የሐይማኖት የፖለቲካ ጉዳዮች የመሳሰሉ ችግሮቻችን ጣራ አልፈው በሄዱበት በአሁኑ ስዓት ለዚህ መድሓኒት የሚቀምም ኬሚስትሪ የት ይኖር ይሆን ?ብየ ጠየቅኩኝ።
አንዳንዶቹ ላቦራቶሪው አፍ ውስጥ ያለው ምላስ ነው።እሱማ ባይሆን የሚያጓጉ የቃላት የመድሓኒት ፍሬ መሪያችን፣አክቲቪስቶችና የሚድያ ሰዎች ባይወረውሩልን ኖሮ ተላልቀን ነበር ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ደህና የነበርነው የተለያየን በማን ሆነና ነው ይሉናል።በሱም አልተግባባንም።በቅርቡ አንድ ሰው የዚህ አገር ቤተሙከራው፣ኬሚስትሪው፣ቅመሙና ቀማሚውም እኔ ነኝ ባይ መጣ ሲባል እሰየው ዋናው ጉዳይ መድሓኒቱ ነው ስንል ለካ ሰውየው ጃዋር ነበር።ቄሮ ያደራጀሁት እኔ፣የሚመራው በኔ፣ኦሮምያን መገንጠል የምችለው እኔ ካልተገነጠለችም በኔ፣ወያኔን የጣልኩ እኔ መመለስ ከፈለገም ውይይቱ ከኔ ሲለን ቆይቷል። ከቅርብ ግዜ በፊት ደግሞ “እኛ” የሚል ጨምሮበታል።እኛ ሲል ኦሮ-ማራ መስሎኝ ነበር። አይደለም።
“እኛ ኦሮሞዎች ከአድዋ ሶሎዳ እስከ ኃይሌ ፊዳ፣
ከአብዲሳ አጋ እስከ አሁንዋ ጅጅጋ፣
ከደህንነት መከላከያ እንዳው ምን አለፋቹ መላው ኦሮምያ፣
ከሃረር እስከ መላ ጎረቤት አገር፣
ሰላም ያመጣን በማሸበር፣
አረ ተው ግን ትግራይ ተው ና ተደመር ።”
የመሳሰሉ ቅኝቶች በተለያየ ቃለ ምልልሱ ሲነግረን ሁላችንም አድምጠናል።እዚህ ላይ ደጋግሞ የፖለቲካ ሳይንስ በማጥናቱ ምክንያት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መፍትሔ እሱ ብቻ እንደሆነና ከሱ መሻገር ግድ ከሆነ ደግሞ ቁልፉ ኦሮሞ ላይ ፈልጉት እያለ በተደጋጋሚ ምክር ሲለግስልን ከርሟል።በተለያዩ ጉዳዮች የተዘበራረቀ አቋም ሲገልዕ የሚሰማው አቶ ጃዋር ዶ/ር አብይ አጭበርባሪ ስለሆነ ጠ/ሚኒስቴር መሆን አይችልም ሲለን ቀይቶ የለውጥ ኃይሉ ከውስጥ እንዲበቅል እና የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ መንግስት የፈጠርነው እኛ ነን ይለናል።አንድ ቀን የአማራ ሊሂቃን ለለውጡ አስተዋፅኦ አበርክቷል ይልና በሁለተኛው ቀን የአማራ ሊሂቃን አላማቸው ሌላ ነው ብሎ በአደባባይ ሲናገር እንሰማዋለን።የኦሮሞ ህዝብ 90% ኦሮሞ ነው ስለዚህ በክርስትያን ላይ እንዲህ ማድረግ ይችላል ሲል ሰምተናል እንደገና በተመሳሳይ ግዜ ሌላ ብሎናል።በቅርቡ አንዲት LTV የምትሰራ ሴት ጋዜጠኛ አቋም ላይ እንዴት ነህ ? ተሎ የመቀየር ነገር ያለ ይመስለኛል ስትለው “አይ ይህ የትግል ስልት ነው።” ብሎ መልስ ሲሰጣት ሰምቼ አንድ የአዲስ አበባ ልጆች የሚቀልዱት ቀልድ ትዝ አስባለኝ።
የዛሬ አያርገውና በአንድ ወቅት ተሰብስበው የወያኔን አሸናፊነት በተመስጦ እያወሩ እያለ
“እንዳው ግን ወያኔ ምን ብያደርግ ነው እንዲህ ታሪክ የሰራው” ሲል አንዱ ይጠይቅና ከመካከላቸው አንድ ሰውየ “ወያኔ ያሸነፈች በስለላ ነው።በአዲሰ አበባ መወልወያ እያሉ እየዞሩ ይሰልሉ ነበር” አላቸው።ይህንን የሰማ አንድ ወጣት ታሪክ ለመስራት ተነሳስቶ ይስማማኛል ወዳለው ድርጅት ተቀላቅሎ መወልወያ ይዞ ሸገር ላይ ይዞራል፣ አንዲት ሴት ባለ መወልወያ ስትለው አይሸጥም ለስለላ ነው።”አላት እንደሚባለው ነው የሆነብኝ።ይህንን ቀልድ ነው ብለው ነው ያወሩኝ በእውነት የሆነ ነገር ካሆነና ቀልድ ካልሆነ ይቅርታ።
እናም ኦቦ ጃዋር ፖለቲካል ሳይንቲስት ስለሆኑ ስለ ስልትና ስትራቴጂ ምንነት እንዲሁም ስለ እያንዳንዳቸው ትስስር ማስተማር ባንችልም ለሁሉም ግዜ አለው የሚለው ግን መንገር ያስፈልጋል።ስልት ማለት የስትራጂው ማስፈፀምያ መሳርያ ሲሆን ስትራቴጂው በተሟላ ሁኔታ መሳካት አለመሳካት ሳያረጋግጥ ለገበያ አይወጣም የሚል ምክር ቢጤ ጣል ብናደርግ አይከፋም ብለን ነው።ለድፍረታችን ዘመኑ የይቅርታ ነው ከሚል ስለሆነ ይቅርታ ብለናል።እርግጥ ነው ኦቦ ጃዋር ብዙ የአቋም መንሸራተት ብምለከትም ግን በወያኔ ላይ ግን ብዙም አቋማቸው ሲቀይሩ አላየሁም።ሁሌ ንግግራቸው ሲጀምሩ “ዲክታተሩ፣አምባገነኑ፣አረመኔው፣ግዙፉ የወያኔ መንግስት መንግለን የጣልነው” ብሎ ይጀምራል።ትዝ ያለኝ በ“ባላ ነው።ለካ እሱ እንደዛ ካላለ ጀግና አይሆንም።ማንን አሸንፎ ጀግና ይሆናል።እውነትህ ነው ልጄ ቀጥልበት።
ኦቦ አሁን ደግሞ ኬሚስትሪው በምሰራበት ግዜ ጌታቸው የሚባል ንጥረ ነገር (Element) ስላገነሁና ለማዋሃድ ስለማይመች ለትግራይ ልሰራው የነበረ መድሓኒት አልሰራም ትቸዋለሁ። እንዳውም ታማ ማየትን እሻለሁ አይነት መግለጫ መስጠቱ ስሰማ ያዘንኩት በሱ ሳይሆን አንድ ሳለ ብዙ፣ሰው ሳለ መልአክ፣አንድ ሜትር ከስድሳ ሰባት ሴንትሜትር እያለ ልክ አልባ፣ ትንሽ እያለ ራስ ዳሽን ተራራ፣እሳት ሊመታው ሲጀምር በሳል እያሉ የጎዱትና ከራሱ ስብእናና ችሎታ ውጭ ለመጥቀምያነት ሲሉ ሌሎች በላዩ ላይ የገጠሙለትን ሶፍት ዌር ለጉዳት እንዲጠቀሙበት የገፋፉትንና ያሳበዱትን ነው።
ወደ ዋናው ጉዳያችን ለመመለስ አገሪቱን እያስተዳደርን ነን ብለው የሚያስቡ እነ ዶ/ር አብይ ነገሩ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ጓያው ከአተሩ፣ስንዴው ከእንክርዳዱ፣አረሙ ከቡቋያው ወዘተ ተደባልቆ አቅጣጫው ጠፍቶባቸዋል። ችግሩ ያለው አሳዳሪዎቻቸው በሰጡዋቸው ማስታወሻ ቅደም ተከተል በማዛነፋቸው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ፣በእነ ጃዋር እና መሰሎቹ የተሳሳተ የቅመማ ውጤትይሁን አይሁን እና ከሌላም ፈልገው ሲያጡት ሁል ግዜ ለክፉ ግዜ መጠባበቅያ የሆነች ከጠረጴዛ ላይ ቀኝ አቅጣጫ የምትቀመጥ ፋይል አለች።ህወሓትና ትግሬ ። እናም አሁምን አገሪቷ ውጥንቅጧ እየወጣ ባለበት ስአት አብሮና ተባብሮ ትክክለኛ የመድሃኒቱ ኬሚስትሪ ማእከል እንደመፈለግ “መደመር ትግራይን ሳይጨምር” የሚል ፈሊጥ በጃዋርኛ “ስልት”ይዘው ከሃዲዱ ባሻገር ሲሽከረከሩ እያየን እንገኛለን። ታድያ ዛሬም ግዜ እየጠበቁ፣ ነገሮች እያቀዘቀዙና እያሞቁ የሰኔ 16 እንደ ዘለአለም የችግር መፍቻቸው አድርገው ለመጠቀም አሰልቺ በሆነ ሁኔታ ከአጀንዳው ለመውጣትና ወደ ስራ ለመግባት አለመፈለጋቸው እያየን ነው። የዚህ ችግር ባለቤት ግልፅ በሆነበትና ባለቤቱም ተለይቶ ለፍርድ በቀረበበት ሁኔታ የትላንትናው የጠቅላይ አቃቢ ህግ ሌላ የገመድ ጉተታ መጫወት የፈለጉ የሚያሳይ መግለጫ፣ በምርመራ ስም ግዜው እየተጓተተ ወደ አሁኑ ጉባኤ የደረሰበት ሁኔታ፣የጃዋር የትላንትናው የመቀሌ አልሄድም ምክንያትና ትንተና ሁሉም በአንድ ግዜ ለአንድ ግልፅ አላማ የሆኑ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ ለሰበር ዜና መዘጋጀት ግድ አይመስላቹም ? በጉባኤውስ ሌላ ሰበር ዜና ይኖር ይሆን ? ሰላም ለኩሉ ከአዲሰ አበባ።