በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ቄለም በምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጅ እንደሚሉት ከሆነ በሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና በኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎች መካከል ዛሬ ጠዋት ግጭት ነበር።
ነዋሪው እንደሚሉት የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን የያዙ ስድስት ኦራል መኪኖች ዛሬ ጠዋት ወደ ከተማዋ ገብተዋል።
”እንደ መትረየስ ያሉ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድምጾች ሲተኮሱ ይሰማል። ትናንት ቤጊ ወረዳ ውስጥ ከፍተኛ ውጊያ እንደነበረ ሰምተናል። ዛሬ ጠዋት ቄለም ከተማ ግጭት ነበር።” እኚህ የከተማው ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ ተሽሽገው ይገኛሉ።
ጊዳሚ ወረዳ ግራኝ ሶንካ በምትባል መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሌላኛው ነዋሪ ከትናንት እሁድ ጀምሮ የተኩስ ድምጽ ሲሰሙ እንደነበረ ይናገራሉ።
”ከትናንት ጠዋት ጀምሮ በቤጊ እና ቄለም ወረዳዎች መካከል ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ነበረ። እንደሰማነው ከሆነ ግጭቱ በሃገር መከላከያ እና በኦነግ ሠራዊት አባላት መካከል ነው” ይላሉ። ከእኚሁ ነዋሪ እንደሰማነው እሳቸውን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ከነቤተሰባቸው ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሽሽተዋል።
የቄለም ወለጋ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ታመነ ኃይሉ በበኩላቸው በዞኑ ውስጥ በሃገር መከላከያ እና በኦነግ ሠራዊት አባላት መካከል የተደረገ ምንም አይነት ግጭት የለም ይላሉ። ”ኦነግ ትጥቅ መፍታት የለበትም የሚሉ ሰላማዊ ሰልፎች በቅርቡ ተካሂደዋል። ሰልፎቹም በሰላማዊ መንገድ ተጠናቀዋል። ከዚህ ውጪ ምንም አይነት ግጭት የለም። በፌስቡክ ላይ የሚወራ ወሬ ነው” ብለዋል።
አቶ ታመነ የሃገር መከላከያ ሠራዊት በዞኑ ውስጥ ለምን በስፋት ተሰማራ ተብለው ለተጠየቁት ”ከዚህ ቀደምም የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በስፋት ተሰማርተው ይገኛሉ። ምንም የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም። ጊዳሚ ወረዳ ለደቡብ ሱዳን ድንበር ቅርብ ናት ለዚህም ነው የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በቦታው የሚገኙት” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ታመነ ”ኦነግ ትጥቅ መፍታት የለበትም” ተብሎ በተወጣው ሰልፍ ምክንያት ዛሬ ጠዋት ድረስ በዞኑ አንዳንድ ከተሞች መንገድ ዝግ ሆኖ ቆይቷል። መንገድ ለማስከፈት ኃይል ከመጠቀም ይልቅ በሃገር ሽማግሌዎች አማካኝነት መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።
በሌላ በኩል የደምቢዶሎ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ክብረት ዋቅጋሪ ትናንት ምሽት ሦስት የፖሊስ አባላት በቦንብ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታላቸው እንደመጡ ይናገራሉ።
”ከለበሱት የደንብ ልብስ መረዳት እንደቻልኩት የፖሊስ አባላት ናቸው። ምናልባትም የደንቢ ዶሎ ከተማ ፖሊስ አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም። ሦስቱም በቦንብ የተጎዱ ሲሆን፤ እግራቸው ላይ እና ጀርባቸው ላይ ክፉኛ ቆስለዋል። የቦንቡ ፍንጣሪ ሰውነታቸው ውስጥ ይገኛል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ይህንን ሁኔታ በተመለከተ ከኦሮሚያ ክልል ሃላፊዎች፣ ከሃገር መከላከያ ሠራዊትም ሆነ በቅርቡ ከተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
የኦነግ ባለስልጣናትም በክስተቱ ላይ ለጊዜው አስተያየታቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።