ጠ/ሚንስትር ኣብይ ኣህመድ ባነኑ እንዴ?
ጠ/ሚንስትር ኣብይ ኣህመድ በኣራት ወራቸው የባነኑ ይመስላሉ። ፈረንጆቹ Better Late Than Never እንደሚሉት ዜጎች በኣደባባይ በስቅላት እስኪገደሉ ድርስ የዘገዩ ቢሆንም የህግ የበላይነት መከበር የግድ እንደሚል ዛሬ መግለፃቸው ጥሩ እርምጃ ነው ብለን እንወስዳለን። ኣሁንም ጠ/ሚንስትሩ ያልባነኑበት ነገር ግን ኣለ። ህገ መንግስትን በሚጥስ ኣግባብ በየክልሉ እጅ ማስገባታቸው ለችግሩ ትልቅ ኣስተዋፅኦ እያደርገ መሆኑን ነው። ወደ ስልጣን በወጡ ሳምንታት ከመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደርጉት ውይይት ህዝብ ከተነሳ ወታደርና መድፍ ሊያቆመው እንደማይችል መናገራቸው እናስታውሳለን። ሆኖም ይህንን ኣባባል በሚጣረስ መልኩ ኣሁን ችግር ኣፍጥጦ ሲመጣ እንደመፍትሄ ወታደሩ ላይ መንጠላጠላቸው የማይቀር ሆነ። በእርግጥ ኣሁን ኣገሪቱ ክገባችበት ቀውስ ኣንፃር ሲታይ የመከላከያ ሰራዊቱ ሚና የሚጠይቅ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለምፍታት ከተፈለገ ግን ቀዳሚ ስራ መሆን ያለበት የችግሮቹን ስረ መስረት እና ጊዚያዊ መንሲኤ የሆኑትን ነገሮች ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።
ዶ/ር ኣብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ ኣንዳንድ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጥሩ ነገሮች ማድረጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ኣውቀውት ይሁን ሳያውቁት፣ የግላቸው እና የቡዱናቸው ስሜት ለመከተል በመፈለግ ይሁን ኣይሁን፣ በራሳቸው ይሁን በሌሎች ሃይሎች (የውስጥና የውጭ) ተገፋፍተው ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የኣገሪቱ ህልውናን የሚፈታተን ኣቅጣጫ በመከተላቸው ምክንያት ኣገራችን ላለፉት 27 ኣመታት ባልታየ ኣኳሃን ኣስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ገብታለች። የዚህ መገለጫ የሚሆነው በክልሎች እና በፌደራል መንግስቱ የቆየውን መተማመን በእጅጉ እንደተሸረሸር እያየን። በብሄሮች መካከልም ቀላል የማይባል ውዥንብርና ስጋት እንደተፈጠረ ግልጽ ነው። ይህ የሆነው ደግሞ ጠ/ሚንስትሩ እና ተከታዮቻቸው እንደሚሉን ለውጥ በማይፈልጉ ሃይሎች (መኖራቸው ኣጠያያቂ ሆኖ) የተፈጠረ ሳይሆን እሳቸውና ቡድናቸው በተከተሉት የተሳሳተ ስሌት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል።
ለምሳሌ በሶማሌ ክልል የተከተሉት ህገ መንግስታዊነት የጎደለው እና የሃይል መጠቀም ኣካሄድ ተነፃፃሪ ሰላም የነበረውን ክልል ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ኣስገብቶ ያን ሁሉ ጉዳት ሊደርስ ችሏል። ይህ ክልል በኦሮሚያ ድንበር ከነበረው ቀውስ በስተቀር ኣሁን በታየው መልኩ እንዳልነበረ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ጠ/ሚንስትሩ የሃይል እርምጃ እንዲወሰድ ሰራዊት ባይሰማሩ እና ሌላ ሰላማዊ መንገድ ቢከተሉ ኖሮ ያ ሁል ውድመት፣ መፈናቀልና የሰው ሂወት መጥፋት ኣይፈጠርም ነበር። የሚያሳዝነው ደግሞ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ምክርቤት ሰብስቦ ኣገር ለመገንጠል ሲመክሩ ነበር የሚል ክሴታ በመንግስት ሚዲያዎች የቀረበ መሆኑን ነው። ኣንቀፅ 39 በህገ መንግስቱ ያስቀመጠ ኣገር እንዲህ ያለ ተቃርኖ ውስጥ መግባቱን ላስተዋለ ዜጋ የኣመራሩን ኣቅመ ቢስነት ቁልጭ ኣድርጎ የሚያሳይ ነው።
ኣሁንም ጠ/ሚንስትሩ እጃቸ በማስረዝም በየክልሉ የሚገኙትን የህዝብ ተመረጭ ፖለቲከኞችን ማውረድና መሾም ስልጣን እንደሌላቸው ተገንዝበው በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች የፈጸሙትን ስህተት እንዳይደግሙት በግልፅ ሊነገራቸው ይገባል። ኣኩራፊ ቡድኖችን እየሰበሰቡ ክልሎች እንዲበጠበጡ ማድረግ ስርኣት ኣልበኝነትን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን ፍጹም ብስለት የጎደለው ኣካሄድ እና ዘመን ያለፈበት የፖለቲካ ጨዋታ ነው። በዚህ ኣመት ውስጥ በኦሮሚያ ለተፈጠረው ቀውስ ለማርገብ ተብሎ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ክልሉ የገባ ጊዜ በክልሉ ባለስልጣናት የተፈጠረውን ቁጣ የምናስታሰው ነው። የባእድ ኣገር ሰራዊት የወረራቸውን ያክል ከፍተኛ ውግዘት እና የኦሮሞ ህዝብ ተደፈረ በሚያሰኝ መልኩ የተለያዩ ቅስቀሳዎች ሲካሄድበት እንደነበረ እየታወቀ በሶማሌ ክልል እንዲህ ኣይነት የተሳሳተ እርምጃ ወስዶ የተለየ ምላሽ መጠበቅ ህግን ያልተከተለ ድርብ መለኪያ ነው ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለውን የፖለቲካ ቀውስ ያለመገንዘብም ጭምር ነው። ህገ መንግስቱን በቅጡ የሚረዳ ኣንድ ኣመራር ክልሎችን ሳያማክር ታጣቂ ሃይል በኣይሮፕላን መላክ ከባድ የፖለቲካ ስካር ስለሆነ ይህ በፍጥነት መብረድ ይኖርበታል።
በመሆኑም ክልሎችም ሆኑ ዜጎቻቸውም እንዲህ ኣይነት ተግባር ከህገ መንግስትም ሆነ ዘላቂ ሰላምና መተማመን ከመፍጠር ኣንፃር ኣፍራሽ ሚና እንዳለው ተገንዝበው ይህ ኣካሄድ እንዲቆም በግልፅ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ይህ የተሳሳተ ኣካሄድ ካልቆመ ግን ድምር ውጤቱ ለማናችንም የሚበጅ ኣይሆንም። ኣገር ከፈረሰ ኣሸናፊ የለምና እሳቸውም ሆነ ቡድናቸው የኪሳራው ኣካል እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። ጠ/ሚንስትሩ ኣሁን መባነናቸው ካልቀረ እስከ ኣሁን የተከተሉት የጥፋት መንገድ በፍጥነት ማረም ይገባቸዋል። በዚህ ኣጋጣሚ ከኤርትራ መንግስት ጋር እየተደረገ ያለውን ፈር የለቀቀ የኣየር-በኣየር ጨዋታ ህዝቡ ኣይገነዘበውም ብሎ ማሰብ ያለኣዋቂነትን ነው የሚያሳየው። ይህ ኣደገኛ ኣካሄድ ጊዚያዊ ነጥብ ለማስቆጠር የሚጠቅም ሊሆን ቢችልም ዘላቂ ኣደጋ የሚያስከትል መሆኑን ግን መገንዘብ የግድ ይላል። ኣንድ ሉኣላዊ ኣገር የሚያስተዳድር መንግስት ወይም በስሩ የሚገኙ ክልሎች ከሌላ ሉኣላዊ ኣገር መንግስት ጋር በመወገን በራሱ ግዛት ያለ ኣንድን ክልል ላይ ማሴር ያልተለመደ ኣካሄድ ከመሆኑም ኣልፎ የለየለት ክህደት በመሆኑ የራስን ታሪክ ሳያበላሹ በፍጥነት ሊታረም ይገባል።
በመጨረሻም ፍቅርን እየሰበከ ጥላቻ፣ ቂም፣ ክህደት፣ ውሸት፣ መከፋፈል፣ ኢህገ መንግስታዊ እና የጉልበት መንገድ እንደ ኣቅጣጫ የሚከተል ኣመራር መሪ ሊሆን ስለማይችል ይህ ኋላ ቀር ኣካሄድ እንደማይጠቅም ተረድተው የኣፋር ኣባቶች የመከሩዋቸውን የመሪነት ብቃት እንዲላበሱ ላስታውሳቸው እፈልጋለሁ። መሪ ማለት፣ ከስሜታዊነት ነፃ የሆነ፣ ሁሉንም በእኩል የሚያይ፣ ሁሉንም በእኩል የሚያዳምጥ፣ ሆደ ሰፊ፣ ታላቆችን የሚያከብር፣ ቃሉን የማያጥፍ እና ኣስተዋይ ሲሆን ነው።
ቸር ይግጠመን
ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ
ነሃሴ 2010 ዓ/ም