አዲስ አበባ፣ ሰኔ፣ 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሀና ማርያም አካባቢ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስን በመልበስ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብርና መጠኑ ያልታወቀ ዶላር ዘርፈዋል የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ግለሰቦቹ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
ከላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፥ ተጠርጣሪዎቹ በትናንትናው እለት በላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያም ተብሎ በለሚጠራው አካባቢ ከቀኑ ስድስት ሰአት ላይ ነው ዝርፍያውን የፈፀሙት።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዝርፊያው በሚፈፀምበት ጊዜ አንድ ግለሰብ ያሰማውን የድረሱልኝ ጩኸት ተከትሎ በአካባቢው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለፖሊስ ባደረጉት ጥቆማ ነው።
ገንዘቡን ተዘርፏል የተባለው ግለለሰብ ላይ በተደረገበ ምርመራ “የተዘረፍኩት ገንዘብ መሬት ለመግዛት ያዘጋጀውት ነበር” ብሏል።
ሆኖም ግን በተደረገው ማጣራት ገንዘቡ ለህገ ወጥ ለዶላር ምንዘራ ስራ ሊውል እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመላከታል።
በዝርፊያው በመሳተፍ ብሩን ሰውሯል የተባለ ሌላ ግለሰብን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስን ለብሰዋል የተባሉ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የፌዴራል ፖሊስ አባል ናቸው ወይስ አደለም የሚለውን ጉዳይም በመጣራት ላይ ይገኛል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዜኑ ጀማል ከፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ተጠርጣሪዎቹ ትክክለኛ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ናቸው በሚለው ጉዳይ ገና እየተጣራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ዜይኑ እንደተናገሩት፥ በትናንትናው እለት በአካባቢው በሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ መኖሪያ ካምፕ በተደረገ ማጣራት በወቅቱ አበላት አለመውጣታቸው ነው የተገለጸው።
በአሁን ወቅት ምርመራ የቀጠለ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ፥ ዘረፈዋል የተባሉ ገለሰቦች የፌዴራል ፖሊስ አባል ከሆኑ በግልጽ ለህበረተሰቡ እንደሚያሳወቁ ተናግረዋል።