አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታሕታይ አድያቦ ወረዳ ነዋሪዎች የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይን አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም ሰለማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
ነዋሪዎቹ፥ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጀርስ ስምምነትና የድምበር ኮሚሽን ውሳኔን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን በመቃወም ነው ዛሬ ረፋዱን ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱት።
ዛሬ በተካሄደው ሰለማዊ ሰልፍ፥ “ሰላም በሰላም እንጂ መሬትን ቆርሶ አሳልፎ በመስጠት አይገኝም፤ የዓዲ ፀፀርና ባድመ መሬት የኢትዮጵያ እንጅ የኤርትራ ሆኖ አያውቅም፤ የኢትዮጵያ ልጆች የወደቁበት መሬት አሳልፈን አንሰጥም” የሚሉ መልእክቶች ያነገቡ መፎክሮች ተደምጠዋል።
በሰልፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፥ መንግስት ከህዝብ ጋር መወያየትና ውሳኔውን ማስተካከል እንዳለበት ሰልፈኞቹ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በኢትዮ- ኤርትራ ጉዳይ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ በመቃወም የባድመ ከተማ ነዋሪዎች ትናንት ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት ዓርብ እለትም፥ ከዓገረሎኸማ፣ እንዳልጌዳ፣ ወርዓትለ፣ ዓሊተና፣ ሓራዘ ሰብዓታ፣ እንዳሞሳ፣ ደውሃን እና ዓራዕ ቀበሌዎች የተውጣጡ የኢሮብ ወረዳ ነዋሪዎች ሰለማዊ ሰልፍ በማካሄድ ውሳኔውን ተቃውመውታል።
በክብሮም ተስፋይ