አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን ስራ ለማስጀመር በአማካይ እስከ 10 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን በማስመልከት ከትናነት ጀምሮ በአድዋ ከተማ እየተካሄደ ባለ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ላይ ነው ይህ የተባለው።
በመድረኩ ላይ ዩኒቨርሲቲውን ስራ ለማስጀመር የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚረዱ የተለያዩ አመራጮችም ይፋ ተደርገዋል።
ከእነዚህም ወስጥ አህጉራዊ ንቅናቄ መፍጠር፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከተጓዦቻቸው ገንዘብ እንዲሰበስቡ ማድረግ፣ የግሉ ዘፍር የራሱን አስተዋፅኦ እንዲወጣ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ታዋቂ የስፖርት ሰዎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ እና አህጉራዊ የስፖርት ውድድሮችን ማዘጋጀት እና ፓን አፍሪካኒዝምን የሚያቀነቅኑ ሙዚቀኞችን በመጠቀም ዓለም አቀፍ ኮንሰርት ማዘጋጀትም በአማራጭነት ተቀምጧል።
በቀጣይም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች አዘጋጅ ኮሚቴ የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ዝግ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲን ተቋማዊ ቅርፅ ለማስያዝ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከትናንት ጀምሮ በአደዋ ከተማ ሲካሄድ ቆይቷል።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፥ በአድዋ የሚገነባው የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ታሪክና የፓን አፍሪካኒዝም የልህቀት ማዕከል እንደሚሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።
የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፥ የአድዋ ጦርነት ለአፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ ትልቅ ድል የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።
በአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችም የወቅቱን የአፍሪካ ችግር በመለየት ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጡ ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱበት ይሆናልም ብለዋል በንግግራቸው።
በትናንትናው እለት የተጀመረው ዓለም አቀፍ ጉባዔው የአድዋ ጦርነት የተካሄዱባቸውን ስፍራዎች በመጎብኘት ማምሻውን ተጠናቋል።
በስላባት ማናዬ