አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 17 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጀት (ኦሕዴድ) 28ኛ አመት የምስረታ በዓልን አክብረዋል።
የምክር ቤት አባላቱ እያካሄዱ ካለው መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን በዛሬው እለት የኦሕዴድን ምስረታ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች አክብረውታል።
የምስረታ በዓሉን ለትግሉ ሰማዕታት የህሊና ፀሎት በማድረግና ሻማ በማብራት አክብረውታል።
የኦህዴድ 28ኛ አመት የምስረታ በዓል በዛሬው እለት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በተለይትም በኦህዴድ ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በፓናል ውይይት ነው ተከብሮ የዋለው።
በበዓሉ አከባበር ላይ ኦህዴድ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄን ለመመለስ እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ድርጅቱ ባለፉት ጊዜያት ባካሄዳቸው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች የህዝቡን ጥያቄ እየመለሰ መምጣቱም በዚህ ወቅት ተጠቅሷል።
ባለፉት ጊዜያት ባለፈባቸው ሂደቶችም ህብረተሰቡ በድርጅቱ ላይ እምነት እንዲጥል ማድረግ መቻሉም ተነስቷል።
በተለይም ድርጅቱ ውስጣዊ ችግሮቹን ለመፍታት ባደረገው ጥልቅ ተሃድሶ የኦሮሞን ህዝብ አንድ ማድረግ ህብረተሰቡ በድርጅቱ ላይ እምነት እንዲጥል አድርጓልም ነው የተባለው።
ኦህዴድ በቀጣይ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሰራ የገለጸ ሲሆን፥ በሂደቱም ጠንካራ አመራር፣ አባላትና የህብረተሰቡ የተግባር አንድነት ያስፈልጋል ብሏል።
በበዓሉ ላይ የድርጅቱን ምስረታ፣ ታሪካዊ ዳራና የትግል ሂደት የሚያሳይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።