አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለቀናት ስብሰባውን ሲያካሂድ የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግንባሩ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያስገቡትን መልቀቂያ መቀበሉን ተከትሎ ነው ምክር ቤቱ ምርጫ በማካሄድ ተተኪ የመረጠው።
ዶክተር አብይ አህመድ ማን ናቸው?
የትውልድ ስፍራ፦ ጅማ ዞን
የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በትራንፎርሜሽናል ሊደርሺፕ እና ቼንጅ፣ ማስተርስ ኢን ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እና በክሪፕቶ ግራፊ እንዲሁም የዶክትሬት ትምህርታቸውን በ“ፒስ ኤንድ ሴክዩሪቲ” አግኝተዋል።
የስራ ልምድ፦ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፣ የፌደራል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውስጥም በምክትል ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም የኢፌዴሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆኑ አገልግለዋል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ በመሆን ሰርተዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ ሊቀመንበር ናቸው።