Widgetized Section

Go to Admin » Appearance » Widgets » and move Gabfire Widget: Social into that MastheadOverlay zone

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ይቆያል


አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት እንደሚቆይ የመከላከያ ሚኒስትሩ ገለፁ።

ሚኒስትሩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው እንዳሉትም፥ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት ተፈጥሮ የዜጎች ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ እየጠፋና ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ሀብት እና ንብረት በቀላሉ እየወደመ ነው።

በተጨማሪም የህዝቦች ለዘመናት በመከባበር እና በመተሳሰብ አብሮ የመኖር ባህሉን የሚሸረሽሩ ቅስቀሳዎች እና አልፎ አልፎ ብሄርና እምነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሲያጋጥሙ ተስተውሏል ነው ያሉት።

እነዚህ ሁኔታዎችም ህዝቡና መንግስት ከሚሸከሙት በላይ እየሆኑ መጥተዋልም ብለዋል።

በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሀገሪቱንና የህዝቦቿን ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅና የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ለማስከበር በመላው ሀገሪቱ ተፈፃሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ነው ያስታወቁት።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚወሰዱ እርምጃዎች

· ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ፣ የህዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ማንኛውም ሁከት እና ብጥብጥ በህዝቦች መካከል መጠራጠርን እና መቃቃርን የሚፈጥር ይፋዊ ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን፣ ፅሁፍ ማዘጋጀትን እና አትሞ ማሰራጨትን፣ ትእይንት ማሳየትን፣ በምልክት መግለፅን ወይም መልዕክትን በማንኛውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግን ይከለክላል።

· ማንኛውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም ደግሞ እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል፣

· የህዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ሲባል የአደባባይ ሰልፍና ሰልፍ ማድረግን፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን ይከለክላል።

· በህገመንግስቱና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን የጠነሰሰ፣ የመራ፣ ያስተባበረ፣ የጣሰ ወይም በማንኛውም መንገድ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈ ወይም ተሳትፏል ተብሎ የሚጠረጠር ማንኛውም ሰውን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ያደርጋል። ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በመደበኛው ህግ ተጠያቂ ያደርጋል።

· ወንጀል የተፈፀመባቸውና ሊፈፀምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ ማናቸውንም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበር እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ማስቆም፣ ማንነቱን መጠየቅ እና መፈተሽ ይችላል።

· በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ እቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት መቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ተጣርቶ ለባለመብቱ ይመለሳል።

· የሰዓት እላፊ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል።

· ለተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ እንዲሆም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ ወደተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ያደርጋል።

· የተቋማትን የመሰረተ ልማትን የጥበቃ ሁኔታ ይወስናል።

· የህዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሳሪያ ወይም ስለት፣ እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች ለይቶ ይወስናል።

· በሰላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን ከክልል እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል።

· ብሄር ተኮር በሆነ ወይም በሌሎች ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ከክልል መንግስታት እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበር ወደ ቀድሞ መኖሪያ ስፍራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙና ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ድጋፍ ያደርጋል።

· ህዝብ የሚገለገልባቸው የአገልግሎት ተቋማት፣ የንግድ ስራዎች ወይም የመንግስት ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ተገቢውን ጠበቃ ያደርጋል።

· ይህን ተላልፎ አገልግሎት ያቋረጠ ማንኛውም ሰው በህግ ተጠያቂ ይሆናል።

· የመሰረታዊ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች አቅርቦት የዝውውር እና የስርጭት ደህንነትን ያረጋግጣል።

· የትራንስፖርት ፍሰት ደህንነትን ይቆጣጠራል፤ ያረጋግጣል።

· በትምህርት ተቋማት የመማር እና ማስተማር ሂደት ከሚያውኩ ተግባራት የፀዱ እንዲሁም መደበኛ ስራን የሚያስተጓጉሉ እንከኖች እንዳይፈጠሩ ይሰራል።

· ህገመንግስቱ እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር፣ ከአደጋ ለመጠበቅ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች ይወስዳል።

እነዚህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮምንድ ፖስት የሚወሰዱ አርምጃዎች ናቸው ብለዋል።

እነዚህ እርምጃዎች ቀጣይ በሚወጡ የአፈፃፀም መመሪያዎች በዝርዝር የሚቀመጡ መሆኑንም አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ተናግረዋል።

ኮማንድ ፖስቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን፣ የደህንንት ፅህፈት ቤትን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩን እና በየክልሉ ያሉ የጸጥታ ምክር ቤት አባላት እና ሌሎችንም እንደሚያካትት ተናግረዋል።

በመግለጫቸው ላይ እንዳሉትም፥ አዋጁ በ15 ቀናት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርብ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም እየታየ ይራዘማል።

ሚኒስትሩ “በሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ይመሰረት ይሆን” በሚል ለቀረበ ጥያቄም፥ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠ በመሆኑ የሽግግር መንግስት መቋቋም አያስፈልግም ብሏል።

“የሲቪል መንግስቱን ወታደሩ ይረከባል” በሚል የሚነሳ ስጋትንም አቶ ሲራጅ ውድቅ አድርገዋል። ሰራዊቱ ከምን ጊዜውም በማል በህገመንግስቱ የታነፀና የተቀረፀ ህዝባዊ ሰራዊት በመሆኑ ለህገመንግስቱ መከበር በፅናት የቆመ ነው ብለዋል።